Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የአፍሪካውያን የኑሮ አለኝታ ነው – የኬንያ የታዳሽ ኃይል ማኅበር

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 4 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የአፍሪካውያን ኑሮ ለማሻሻል የሚረዳ ፕሮጄክት መሆኑን የኬንያ የታዳሽ ኃይል ማኅበር አስታወቀ፡፡

የማኅበሩ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አንድሪው አማንዲ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቡን መጠናቀቅን ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ማኅበረሰብ ማየት የሚፈለጉት ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ኬንያ ከብክለት ነጻ የሆነ አረንጓዴ የኃይል አማራጭ ከኢትዮጵያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኘች መሆኑንም አመላክተዋል።

እንዲያውም ከኢትዮጵያ የሚመነጨው ከብክለት ነጻ የሆነ ታዳሽ የውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል ኬንያ ወደ አካባቢ የምትለቀውን የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን በ10 በመቶ እንድትቀንስ ያስችላታልም ነው ያሉት።

“ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ኬንያ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባውን የኃይል መጠን ትጨምራለች ፤ ለዛም ነው በጉጉት የምንጠብቀው” ሲሉም ነው ተሥፋቸውን የገለጹት – አንድሪው አማንዲ

አንድሪው አማንዲ በአሁኑ ጊዜ አፍሪካ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እጥረት እያጋጠማት መሆኑን በማንሳት፥ አኅጉሪቱ በቀዳሚነት ይህን ክፍተቷን ለመሙላት የተፈጥሮ ሐብቷን መጠቀም አለባት ብለዋል፡፡

ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ምሳሌ መሆን የሚችልና አፍሪካን በኃይል አማራጭ በማስተሳሰር የበርካቶችን ሕይወት ለመቀየር የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጄክት በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት እና ተፅዕኖ እንደማያደርስም አስገንዝበዋል።

ለዚህ ጥቅም እንጂ ጉዳት ለሌለው የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሁሉም ጥብቅና ሊቆምለት እንጂ የሚናፈሰውን አሉታዊ ትርክት ሊያራግብ እንደማይገባም አውስተዋል።

በአህጉሪቱ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላትም ንጹህና የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምን ማስፋፋት ይገባልም ነው ያሉት በንግግራቸው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ውኅደት ለመፍጠር ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.