Fana: At a Speed of Life!

ፀሎተ ሐሙስ በተለያዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓቶች ታስቦ ዋለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፀሎተ ሐሙስ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በዛሬው ዕለት በተለያዩ ሐይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ታስቦ ውሏል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬዋ እለት ዝቅ ብሎ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ፍጹም ትህትናን እና ታዛዥነትን ማስተማሩን በማሰብ ነው በዓሉ የተከበረው፡፡

በዓሉ በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት እንዲሁም በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ታስቦ ውሏል፡፡

በዚህም የህጽበተ-እግር ሥነ-ሥርዓትን ታላላቅ አባቶች ከደረጃቸው ዝቅ ብለው የምዕመናንን እግር በማጠብ የኢየሱስ ክርስቶስን አርአያነት ተከትለው ሥርዓቱን ፈፅመዋል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ቆሞሳት፣ ካህናት እና ምዕመናን በተገኙበት እለቱ በተለያዩ መንፈሳዊ ሥርዓቶች ታስቧል፡፡

በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ፍጹም ትህትናን ያስተማረበትና ዝቅ ብሎ የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበበት በመሆኑ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል።

ፀሎተ ሐሙስ በቤተሰብ ውስጥም ትህትና እንዲኖር የሚያስተምር ሲሆን÷ እርስ በርስ በትህትና መደጋገፍና መረዳዳት የትህትና ትልቅ ምስጢር ስለሆነ ከዚህ ብዙ መማር እንደሚቻልም ተጠቅሷል፡፡

በየሻምበል ምህረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.