ኢትዮጵያ ወንጀልን በመከላከል ለቀጣናው ሰላም እያከናወነች ያለውን ስራ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ድንበር ዘለል ወንጀል እና ሽብርተኝነትን በመከላከል ለቀጣናው ሰላም እያከናወነች ያለውን ስራ አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ ገለጸ።
የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድንበር ዘለል ወንጀሎችንና ሽብርትኝነትን ለመከላከል ለሶስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የምክክር መድረክ የኮሚቴዎች ስብሰባ አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ ፥ ምክክሩ በቀጣናው የሚታዩ ድንበር ዘለል የሰላምና ደህንነት ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በፆታዊ፣ በሽብርተኝነት፣ በሳይበር እና የህግ መተላለፍ ወንጀሎችን የሚመለከቱ ምክረ ሃሳቦች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸውም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሊቀ-መንበርነት በምትመራው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ሽብርተኝነት፣ ድንበር ዘለል የወንጀል ስጋቶችን ለመከላከል ለቀጣናው አገራት የምታደርገው ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በፌዴራል ፖሊስ የብሔራዊ ኢንተርፖልና ዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር ዳይሬክተር ኮማንደር ጸጋዬ ኃይሌ በበኩላቸው÷ በመድረኩ ኢትዮጵያ በህብረተሰብ ተሳትፎ እና ከጎረቤት አገራት ጋር በመተባባር የምታካሂደው የጸረ-ሽብር እና ድንበር ዘለል ወንጀል መከላከል ስራ ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ተሞክሮ መቅረቡን ተናግረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት የኮሚቴዎች ስብሰባ ላይ ከቀጣናው አባል አገራት የተውጣጡ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡