Fana: At a Speed of Life!

ግብረ ሃይሉ የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረሃይል አስታወቀ፡፡

በዓላት ሲቃረቡ ከወትሮው የተለየ የእግረኞች እና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ይስተዋላል፤ ይህንን እንቅስቃሴ ተከትሎ በተለያዩ ስፍራዎች ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ እና የትራፊክ አደጋ እንዳያጋጥም የፀጥታ ተቋማት ሙሉ የሰው ሃይላቸውን በስራ ላይ በማሰማራት ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩበት ወቅት ነው፡፡

በዘንድሮው የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላት ወቅትም ሆነ ከበዓላቱ አስቀድሞ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በተለይም በገበያ ስፍራዎች፣ በመዝናኛ ቦታዎች እና በዕምነት ተቋማት አካባቢ ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የፀጥታ ድባብ እንዲኖር የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ለመወጣት የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

የተሻለ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር እና የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ እንዳያጋጥም የትራፊክ ፖሊሶችና ሌሎች የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚያከናውኑትን ተግባር ህብረተሰቡ ሊደግፈው እንደሚገባ የጠቀሰው የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል፤ ጠጥቶ ባለማሽከርከር፣ የእርድ እንስሳትን በተሽከርካሪ መንገድ ላይ ባለመንዳት እንዲሁም ተገቢውን የትራፊክ ደንብ አክብሮ በመጓዝና ለትራፊክ ፍሰት እንቅፋት ከሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ራስን በማራቅ አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብሏል፡፡

በገበያ ቦታዎች ፣ በትራንስፖርት መጠበቂያ ስፍራዎች እና ሌሎች የህዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ግርግሩን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ወንጀል ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እንደሚኖሩ በመገንዘብ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ የመከላከል ስራውን በትኩረት እንደሚያከናውን ገልፆ ህብረተሰም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡

በዓሉ የሰላምና የደስታ በዓል ሆኖ እንዲያልፍ እና የዕምነቱ ተከታዮች ያለምንም የፀጥታ ሥጋት ያከብሩ ዘንድ በዚህ የፀጥታ ማስከበር ሂደት ውስጥ በአካባቢያቸው ለሰላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከቱ  በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ግብረ ሃይሉ ጥሪ አስተላልፏል።

በመጨረሻም በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች መልካም በዓል እንዲሆን ምኞቱን ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.