Fana: At a Speed of Life!

ምዕመኑ በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳት እንዲያከብር ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)  ምዕመኑ የትንሳዔ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳት እንዲሆን የዕምነት አባቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ የትንሳዔ በዓልን አስመልክተው ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም “የሰው ልጅ ንስሐ ገባ የምንለው ይከተለው የነበረውን ክፉ ተግባር ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጎ በመተው ወደ መልካም ተግባር ሲመለስ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በዓሉን ስናከበርም የተቸገሩትን በመርዳት እና የሀገር አንድነትን በዕርቅ ዘላቂ ለማድረግ ቃል በመግባት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል ባስተላለፉት መልዕክት÷ በዓሉን ስናከብር ለድሆችና ለአቅመ ደካሞች፣ በችግር ውስጥ ላሉ ሰዎች በመለገስ መሆን እንዳለበት አንስተዋል፡፡

የጥላቻን ሐሳብና ንግግር በትንሳዔ የምስራች እንለውጠው ሲሉም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፡፡

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ በበኩላቸው÷ የወጣቶች የነገ ተስፋ ብሩህ የሚሆነው የሀገር ሰላምና አንድነት ሲጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለሀገራችንና ለሕዝባችን ሰላም ቅድሚያ በመስጠት በጋራ እንስራ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.