ትጥቅ ከፈቱ የህወሓት እና የሸኔ ታጣቂዎች ጋር ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን አመራሮችና ተቋሙን ለማደራጀት የተመደቡ አማካሪዎች ትጥቅ የፈቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የህወሓት እና የሸኔ ታጣቂዎች በተሰባሰቡባቸው ካምፖች በመገኘት አወያይተዋል።
ትጥቃቸውን አውርደው በምስራቅ ትግራይ ደሳአ፣ አጉላ እና እዳጋ ሀሙስ ካምፖች የተሰባሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ የህወሓት የቀድሞ ተዋጊዎችን፥ የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን አደራጅ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮች በመስክ ተገኝተው አነጋግረዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የቀድሞ የህወሓት ታጣቂዎች ያሉባቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በዝርዝር የገለፁ ሲሆን ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው ከወጡበት ማህበረሰብ ጋር በመቀላቀል የሰላምና የልማት ሀይል ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ለልዑካን ቡድኑ አሳውቀዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል አማካኝነት ትጥቅ ፈተው በምዕራብ ሸዋ አምቦ አካባቢ ሰንቀሌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ተሰባስበው በተሀድሶ ስልጠና ላይ የሚገኙ ከ2 ሺህ 300 በላይ የሸኔ የቀድሞ ተዋጊዎችን በብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብ/ጀኔራል ደርቤ መኩሪያ የተመራ ቡድን በስፍራው ተገኝተው አነጋግረዋል።
ብሄራዊ የተሀድሶ ኮሚሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 525/2015 ዓ.ም ተጠሪነቱ ለሰላም ሚኒስቴር ሆኖ መቋቋሙን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።