Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሰን፣ አደረሳችሁ!

በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ሥፍራ ተሰጥቷቸው ከሚከበሩ በዓላት መካከል በዓለ ትንሣኤው በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የፍቅር ጥግ የታየበት፣ የዕርቅና የይቅርታ ትርጉም የተገለጠበት፣ ምሕረትና ድኅነት የተረጋገጠበት፣ የአዳም ተስፋ የተፈጸመበት ታላቅ በዓል ነው።

በቀዳሚዎቹ ዘመናት አባታችን አዳም አትብላ የተባለውን ዕጸ በለስ በልቶ የፈጣሪን ትእዛዝ ከተላለፈ በኋላ የሰው ልጅ የአምላክ ፍቅር ርቆት የፍዳ ዘመናትን አሳልፏል።

በዲያቢሎስ ሤራ የተቆረጠው የፈጣሪና የፍጡር ፍቅር ዳግም እንዲታደስ አምላክ ከዙፋኑ ወደ ምድር ወረደ፤ በሰው ቁመትና ወርድ ተወሰነ፤ በደሙ አጥቦ የሰው ልጅን ከዘላለም ርግማን ሊያነጻ ክርስቶስ ታመመ፤ ስድብና ማንጓጠጡን፣ ውንጀላና ግርፋቱን፣ የዓለምን መከራ ሁሉ ያለ በደሉ ተቀበለ። ፍቅር በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ታየ። ፍጹም ፍቅር ከክብር ዙፋን ላይ መውረድን እንደሚጠይቅ፤ እውነተኛ መውደድ በቅድመ ሁኔታዎች እንደማይታጠር ክርስቶስ በተግባር አስተምሮናል።

የትንሣኤ በዓል የዕርቅና የይቅርታ በዓል ነው።

የክርስቶስ ትንሣኤ በአዳምና በእግዚአብሔር መካከል ለዘመናት ተገንብቶ የቆየውን የጸብ ግድግዳ እስከ ወዲያኛው አፈራርሶታል። ጸብ በሰው ልጆች ስሕተት ምክንያት የመጣ ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በማንኛውም አጋጣሚ በሰው ልጆች መካከል ጸብ ሊፈጠር ይችላል።

እንኳን ሰውና ሰው፣ ወንድምና እኅት ይቅርና፤ በፈጣሪና ፍጡር፣ በአምላክና ሰው፣ በመንፈስ አባትና ልጅ መካከልም ተከሥቷል። ዋናው ቁም ነገር የተፈጠረው ጸብ እስከወዲያኛው አራርቆ አለማቆየቱ፤ በዕርቅና በይቅርታ መቋጨቱ ላይ ነው። በትንሣኤው አዲስ የምሕረት ምዕራፍ ተከፍቶ የሰው ልጆች የርግማን ሰነድ ተሰረዘ እንጂ የበዳዩ በደል ተዘርዝሮ ሂሳብ ወደ ማወራረድ አልተገባም።

የተበደለ ፈጣሪ ሳለ ልጁን ለመሥዋዕት የላከው እሱ ነው። ዕርቅ አውራጁም እሱ፣ ይቅር ባዩም እሱ ነው። የዕርቅ ዓላማው ሰላም በማውረድ መከራን ማጥፋት ነውና ተበዳዩ ይቅር ቢል የእሱን ታላቅነት ያሳያል እንጂ ተሸናፊ እንደማያደርገው የትንሣኤው ታሪክ ያስተምረናል።

ዛሬ በትንሣኤው በዓል ሰሞን ሆነን ባለፉት ረጅም ዘመናት በሀገራችን የተፈጠሩ ጸብና አለመግባባቶችን በዕርቅ ስለመቋጨት ማሰብና መወሰን አለብን። በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ የትናንት መቆራቆሶች የነገ ተስፋችንን እንዳያጨልሙ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መክረንና ዘክረን እንቋጫቸው። ከሂሳብ ማወራረድ አባዜ እንውጣ፤ ዳግም በምድራችን የታሪክ ዕዳ የተስፋ ምንዳችንን ቆረጣጥሞ አይብላው። የሐሳብ ልዩነቶች ከጠረጴዛ አልፈው የዐውደ ውጊያ መነሻ እንዳይሆኑ ለስሜቶቻችን ልጓም እናበጅላቸው፤ እልህና ክፋት ውድቀትን፣ ቅንነትና ምክክር ዕድገትን እንደሚያመጣ ዕንወቅ።

ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣

ሀገራችን የትንሣኤዋ ዋዜማ ላይ ነች። የምናያቸው ፈተናዎች የሕማማት ሰሞን ፈተናዎች ናቸው። እንደ ክርስቶስ ትንሣኤ ሁሉ የሀገራችን ብልጽግና እውን እንደሚሆን፣ የኢትዮጵያችን ትንሣኤ እንደሚሳካ ምንም ጥርጥር የለውም።

ይኽ የሚሆነው ግን እንደ ኒቆዲሞስ ተስፋን ሰንቀው ወደ ትንሣኤው ብርሃን የሚገሠግሡ፣ እንደ ዮሐንስ ውዥንብሩን ሁሉ በጽናት የሚያልፉ፣ እንደ ሮማዊው መቶ አለቃ እውነትን በድፍረት የሚመሰክሩ ዜጎች ሲበዙ ነው። ተስፋ ቆርጦ ጨለማው በራሱ ጊዜ እስኪገፈፍ፤ ድቅድቅ ሌሊቱ ተፈጥሯዊ ዑደቱን ጠብቆ እስኪነጋ እጅን አጣጥፎ በመቀመጥ ግን አይሳካም።

የትንሣኤው ጸጋ የግቡን ምንነት እንጂ ሂደቱን እንደማይጠቁም ሁሉ፤ “የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን ከመሆን አይቀርም” የምንለው ጉዞው ቀላል እንደማይሆን በማመን ነው። ስለ ክርስቶስ መምጣት፣ ለአዳም ልጆች የመሥዋዕት በግ ሆኖ ስለመቅረቡና ሞቶ ስለ መነሣቱ አስቀድሞ ብዙ ትንቢቶች ተነግረዋል።

ይሄንን ሁሉ ክደው ግን ከሄሮድስ እስከ ይሁዳ ብዙዎች ትንሣኤውን ለማስቀረት ሞክረዋል። በጉዞው ላይ ሰይፍ፣ ውንጀላ፣ መሳደድ፣ ክህደት፣ አሉባልታ፣ ሽብርና የመሳሰሉት ትንሣኤውን ሊገዳደሩት ሞክረው ነበር። የብልጽግና ጉዟችንም ከዕንቅፋቶች የጸዳ አይሆንም።

በተለይ በተለይ እንደ ይሁዳ ሀገርን በሽርፍራፊ ሳንቲም ለመሸጥ የማያመነቱ ሰዎችን ይዘን ጉዟችን ቀላል አይሆንም፤ ዜጎቻችን ቀናውን መንገድ የሚጠቁሙትን ትተው፣ እንደ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ላሉ÷ ቅንነት በጎደለው ዕውቀት ለተሞሉ ሰዎች ሙሉ ጊዜያቸውን መስጠት ከጀመሩ ሩጫችን ወደ ርምጃ መለወጡ አይቀርም። ስለዚህ በብልጽግና ጉዟችን ውስጥ ከፈተናችን በላይ መሆን እንድንችል የፈተናችንን ዓይነትና ፈታኞቻችንን ለይተን ማወቅ እና በጽናት ለመታገል መወሰን አለብን።

መጨነቅና መጠበብ፣ ማወቅና መጠንቀቅ፣ መጽናትና ከክፋት መጠበቅ የሚያስፈልገን የሽግግር ሂደቱ በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞላ በመሆኑ ነው። ትንሣኤ እውን የሆነው አያሌ ተግዳሮቶችን ድል ነሥቶ ነው። መንገዱ ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም። ሕማማት የበዛበት ነበር።

ወደ ተራራ መውጣት ቁልቁለት እንደ መውረድ አይቀልም፤ ላብና ትንፋሽ ይጠይቃል። ወደ ትክክለኛ መዳረሻ የሚወስድን ትክክለኛ መንገድ መርጦ መጓዝን ይሻል፤ ከምንም በላይ በየምዕራፉ የሚገጥሙ እሾህና ጋሬጣዎችን፣ ቋጥኝና አውሬዎችን በሰላም ለመሻገር መተባበርና መደጋገፍ ከተጓዦች ይጠበቃል።

የብልጽግና ጉዞ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት የኅብረት ጉዞ እንጂ ጥቂቶች የሚያሸንፉበት የጥሎ ማለፍ ሩጫ አይደለም። ስለሆነም በትብብር ፋንታ መጓተትን፣ በመደጋገፍ ፋንታ መገፋፋትን ከመረጥን ጉዟችን አንድ ርምጃ ወደፊት መቶ ርምጃ ወደኋላ ስለሚሆን ካሰብንበት ግብ በፍጥነት እንደርሳለን ማለት ዘበት ነው። ትንሣኤው አይቀሬ ነው። ፈተናው ተሸናፊ ነው። የጸናም አሸናፊ ይሆናል።

በድጋሜ መልካም የትንሣኤ በዓል!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሚያዚያ 7፣ 2015 ዓ.ም

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.