Fana: At a Speed of Life!

“በክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጅ ዘላለማዊ ጠላት የሆነው ሰይጣን ተሸንፏል” –  አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ÷ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩት ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ የትንሣኤ በዓል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዓሉን ከኃጢዓት ወደ ጽድቅ፣ ከውርደት ወደ ክብር፣ ከሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነጻነት፣ ከአደፈና ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ አዲስ ማንነት የተሸጋገሩበት፣ ከበዓላት ሁሉ የበለጠ የነጻነት በዓል እንደሆነ አድርገው ያከብሩታል ነው ያሉት፡፡

ክብርና ነጻነት ለሰው ልጅ የተሰጡ የማይገሰሱ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ናቸው ያሉት አፈጉባዔው÷ ሰው የመሆኑ መገለጫዎችና የሰብዕናው መሠረቶች ናቸውም ብለዋል፡፡

በውርደትና በባርነት የሚኖር ሰው ማንነቱን ያጣ፣ ሰብዓዊ ክብሩን የተቀማ፣ ያሻውን እንዳያስብና መሠረታዊ ፍላጎቶቹን እንዳያሟላ የተከለከለ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ያለነጻነት ሰውነት፣ ያለክብር ማንነት እንደማይኖር ጠቅሰው÷ በክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጅ ዘላለማዊ ጠላት የሆነው ሰይጣን ተሸንፏል ብለዋል፡፡

የሰው ልጅም ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገሩን፣ ከባርነት ወደ ነጻነት፣ ከውርደት ወደ ክብር፣ ከጉስቁልና ወደ ልዕልና መመለሱንም በመልዕክታቸው  ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አስከፊውን የጨለማ ዘመን ተሻግረው፣ የለውጥ አየር መተንፈስና የለውጡን ትሩፋቶች ማጣጣም ከጀመሩ ጥቂት ዓመታትን አስቆጥረዋልም ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ ያልተሻገርናቸው ፈተናዎች ቢኖሩም ይህ ወደ ብልጽግና የሚያደርሰን ለውጥ እንዳይሰናከል፣ ብሎም ወደባርነት፣ ውርደትና ጉስቁልና እንዳንመለስ ሁሉም የበኩልን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የትንሣኤው ባለቤት የሆነውን ክርስቶስ ከትንሣኤው አስቀድሞ በመዋዕለ ሥጋዌው ዓለም ንቆታል፤ ዘብተውበታልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሚናገራቸው ቃላት፣ የፈጸማቸው ተአምራት ሁሉ ተቀባይነት አልነበራቸውም ያሉት አፈ ጉባኤ አገኘሁ÷ ሁሉም ለውድቀቱ የሚሆን በትር አነሱበት እንጂ ጥብቅና አልቆሙለትም ብለዋል፡፡

እርቃኑን በቀራንዮ አደባባይ ላይ እንዲቆምና እንዲሰቀል አደረጉት እንጂ አልደገፉትም፤ይሁን እንጂ በሞቱ ሞትን ድል ከነሳ፣ በመቃብሩ ትንሣኤውን ካወጀ ማግስት በኋላ ግን ብዙዎች አምላክነቱንና አስተምህሮውን አምነው ተከትለውታል ብለዋል።

የለውጥ ሀሳብ አፍላቂዎች ማህበራዊ ቅቡልነት እስኪያገኙ ድረስ መከራው እንደሚበረታባቸው  ጠቅሰው÷ሁላችንም ነገሮች ተፈጽመው ባስከተሉት ጥፋትና ውድመት ከመጸጸታችን በፊት አስቀድመን ግራ ቀኙን በአመክንዮ መመርመርና ማስተዋል ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡

ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን አሻግሮ ማየት እንደሚገባ፣ ዛሬ የምናጣጥለውና የምናቃልለው ሀሳብ የነገ መዳኛ ትልማችን ሊሆን ስለሚችል ሕብረብሔራዊ አንድነትን ወንድማማችነትና እኩልነትን በሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባናል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.