Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ፖሊስ ልብስ በመልበስ ንብረት የዘረፉ ተከሳሾች በጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ፖሊስ ልብስ በመልበስ በጦር መሳሪያ በማስፈራራት ከ395 ሺህ ብር በላይ ንብረት የዘረፉ ተከሳሾች ከ13 እስከ 14 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ፡፡

ተከሳሾቹ÷ 1ኛ አሸብር ተስፋዬ፣ 2ኛ አብዲ ሰይድ (ኢ/ር) እና 3ኛ ሰለሞን አየለ መሆናቸው የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ተከሳሾቹ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ሰለፊያ መስጂድ አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ልብስ በመልበስና የጦር መሳሪያ በመያዝ የግል ተበዳይ ሳሊሞ ጀማል ረዳን ግቢ የውጭ በር በማንኳኳት እና ሕጋዊ ሰዎች ነን፣ ሕጋዊ ወረቀት ይዘናል፣ ለፍተሻ ነው የመጣነው በማለት ወረቀቱን ያሳያሉ፡፡

የግል ተበዳይም ይህንኑ አምነው በሩን ሲከፍቱ ተከታትለው በመግባትና በሽጉጥ በማስፈራራት÷ 300 ሺህ 590 ብር፣ ግምቱ 80 ሺህ ብር የሆነ አንድ ሩሲያ ሰራሽ ማካሮቭ ሽጉጥ ከ8 ጥይቶች ጋር እንዲሁም 15 ሺህ ብር የሚያወጣ አንድ ሳምሰንግ ጋላክሲ ሞባይል ይዘው መሰወራቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

በአጠቃላይ 395 ሺህ 590 ብር ዋጋ ያለው ንብረት ዘርፈው በመሰወር በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ሚያዝያ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት በ3ቱም ተከሳሾች ላይ በደረጃ 8 እርከን 34 ስር መነሻ ቅጣት ተይዞ÷ በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሽ ላይ 1 የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው እርከን 33 ስር በማሳረፍ እያንዳንዳቸው በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡

በ3ኛ ተከሳሽ ላይ ደግሞ 2 የቅጣት ማቅለያ ተይዞለት እርከን 32 ስር በማሳረፍ በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.