የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ እስረኞች መፍታትን የተመለከተ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የትግራይ ጊዜያዊ መስተዳደር ካቢኔ የተገኘውን የሰላም ሂደት ለማፅናት በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙትንና ፍርደኛ እስረኞች መፍታትን የተመለከተ ውሳኔ አሳለፈ።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፅሕፈት ቤት ባወጣው መረጃ እንዳስታወቀው፥ ውሳኔው ክልሉን መለሶ በማቋቋም ሂደት ህዝባቸውን እንዲክሱ እድል ለመስጠት ነው።
በመሆኑም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ሚያዝያ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ፥ የእስረኞች ክስ በማቋረጥ፣ ማጣራትን በማንሳት፣ እንዲሁም በይቅርታ እንዲፈቱ እንደወሰነ አስታውቋል።
በፕሪቶሪያ የተደረገውን የሰላም ስምምነት መሰረት በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ተቋቁሞ ወደ ስራ እንደገባ ያስታወቀው ካቢኔው፥ ውሳኔው በፌዴራል መንግስት የተጀመረው እስረኞችን የመፍታት ተነሳሽነት ለማበረታታት እንዲሁም በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የበለጠ መተማመንን በመፍጠር ዘላቂ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያግዝ አስረድቷል።
ውሳኔው በጥብቅ ዲሲፕሊንና በአስቸኳይ እንዲፈፀም ለሚመለከታቸው ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፍትህ ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እና የትግራይ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ማስተላለፉን አመላክቷል።
ውሳኔው ከሚያዝያ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ መሆኑን ገልጿል።