Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ኮሪያ የኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2023 ኢትዮ-ኮሪያ የኢንቨስትመንት ፎረም በደቡብ ኮሪያ ሴዑል ከተማ ተካሂዷል፡፡

በኢትዮጵያ ስላሉ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት ዕድል እና አማራጮች ለኮሪያ ባላሃብቶች ለማሳወቅ ያለመ ፎረም መሆኑ ተገልጿል፡፡

በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው መልካም ወዳጅነት በኢኮኖሚው ዘርፍም የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎች መኖራቸውን፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን፣ ምቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እና የመሰረተ ልማት ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ መኖሩን አብራርተዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ በውጭ ባለሃብቶች ተመራጭ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ያደርጋታል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ቴሬሳ÷ በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ምቹ በመሆኑ የኮሪያ ባለሃብቶች ኢንቨስት የሚያደርጉበት ምቹ ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኮሪያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ፌዴሬሽን ምክትል ሊቀመንበር ጁ ሶርዮንግ (ዶ/ር) ÷ ሀገራቱን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ መናገራቸውን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በፎረሙ ላይ ከ120 በላይ የኮሪያ ባለሃብቶች እና የድርጅት መሪዎች መሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን÷ ፎረሙ በደቡብ ኮሪያ ቡሳን ከተማ ቀጥሎ እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.