የፊቼ ጫምባላላ በዓል ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ “ፊቼ ጫምባላላ” በዓል ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ እንደገለጹት÷ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታና ባለድርሻ አካላት የጋራ ዕቅድ አውጥተው እየተንቀሳቀሱ ነው።
“ህዝባዊ በዓላት ሲከበሩ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ይገባል” ያሉት ኮሚሽነሩ በዓሉ ከሃዋሳ በተጨማሪ በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎችና ከተሞች ስለሚከበር ዝግጅቱ ይህንን ታሳቢ ማድረጉን ገልጸዋል።
ለበዓሉ ከሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች የሚመጡ ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአካባቢው ወጣቶችም በሰላም አምባሳደርነት ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የሰላምና ጸጥታውን ሥራ ያከናውናሉ” ብለዋል።
በተጨማሪም ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በዓሉን በሰላም ለማክበር የሚያስችል ውይይት መደረጉን ኮሚሽነር ሽመልስ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡