Fana: At a Speed of Life!

በሚከናወኑ የልማት ተግባራት ላይ የተጠያቂነት ስርዓት እንዲሰፍን እየተሰራ ነው – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በሚከናወኑ የልማት ተግባራት ላይ የዜጎችን ተሳትፎና ግልፀኝነትን በመተግበር የተጠያቂነት ስርዓት እንዲሰፍን እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ፡፡

በ2015 በጋምቤላ ክልል ምክር ቤት የጸደቀው የዜጎች በጀት መረጃ ሰነድ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ውይይት ተደርጎበታል።

በመድረኩ ክልሉ በ2015 የበጀት አመት ሊፈፅማቸው ካቀዳቸው የልማት ተግባራት 4 ቢሊየንን 542 ሚሊየን 560 ሺህ 719 ብር መመደቡ ተጠቁሟል፡፡

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ÷ በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ተግባራት ላይ የዜጎች ተሳትፎና ግልፀኝነትን በመተግበር የተጠያቂነት ስርዓት እንዲሰፍን እየተሰራ ነው ብለዋል።

የክትትልና ግምገማ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸው÷ በተለይም የገንዘብ አጠቃቀም ችግርና በግዢ አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉ የህግና ደንብ ጥሰቶችን በመለየት ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ኡቦንግ ኡቶው በበኩላቸው÷ የዜጎች በጀት መረጃ ሰነድ ገቢና ወጪ ዕቅዶች ውስጥ የተካተተውን በጀት ማህበረሰቡ በቀላሉ ተረድቶና ተጠቅሞ በልማት ስራዎች ላይ ተሳትፎውን በማጠናከር የተጠያቂነት ስርዓት እንዲሰፍን መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

የቀረበው ሰነድ በክልሉ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈፀም አኳያ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና የልማት አገልግሎቶችን ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የዜጎችን የሚያጋጥማቸውን የመረጃ ክፍተት ለማስተካከል ትኩረት ተሰጥቶ መስራት የሚጠይቅ መሆኑን ያነሱት አመራሮቹ÷ የኦዲት ግኝት ያለባቸው መስሪያ ቤቶችላይ ተጨባጭ እርምጃ ሊወሰድ ይገባልም ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.