Fana: At a Speed of Life!

የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምበላላ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምበላላ እየተከበረ ነው፡፡

በበዓሉ አከባበር ላይ÷ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ የክልል፣ የዞን፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

አቶ ደስታ በአከባበሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ፍቼ የአንድነት ተምሳሌት፣ ፍቅርና አንድነትን የሚያሰርፅ የዘመን መለወጫ ነው ብለዋል፡፡

የፍቼ ጫምበላላ ትውፊት በፍቅር እና አንድነት አብሮ መኖር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ፍቼ ጫምበላላ ማንም የሰው ዘር አብሮ በፍቅር እንዲኖር የሚያስተምር፣ ባህላዊ የአዲስ አመት መቀበያ ቀን ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በዓሉ በሲዳማ አያንቱዎች አቆጣጠር አዲስ አመት የሚበሰርበት ሲሆን÷ የዛሬዋ ቀንም ለአሮጌው አመት ሽኝት የሚደረግባት ናት፡፡

የበዓሉ አክባሪዎች ቡርሳሜ የተሰኘውን ባህላዊ ምግብ ከተመገቡ በኋላ ”ፍቼ ጄጂ” በማለት ይመርቃሉ፡፡ ትርጉሙም  መልካሙ ሁሉ ይግጠመን እንደማለት ነው።

በዛሬው ምሽት የተጣላ ሰው የሚታረቅበት፣ የተለያዩ ባል እና ሚስቶች ተመልሰው የሚገናኙበት እና አዲሱን አመት በአዲስ መንፈስ የሚጀምሩበት እለት ነው፡፡

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሴሴ ጫሊ፣የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የተለያዩ ክልሎች አመራሮች የፊቼ ጫምባላላን በዓል ለመታደም ሐዋሳ ከተማ ገብተዋል።

በጥላሁን ይልማ፣ ብርሃኑ በጋሻው እና ተመስገን ቡልቡሎ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.