Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የንጹሃ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወጪ የንጹሃ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ እያከናወነ መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ÷ በሶማሌ ክልል የሚከሰትን ድርቅ በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችሉ የተለያዩ የንጹሃ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
የግንባታ ስራዎቹ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች እና የገጠር አካባቢዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
 
የገንዘብ ድጋፉ ከዓለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከዋን ዎሽ ፕሮግራም እና ከተለያዩ አጋር አካላት በእርዳታ እና ብድር የተገኘ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
 
የዋን ዎሽ ፕሮግራም አካል የሆኑና በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ መቋቋም የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናታቸው ተጠናቆ ወደ ግንባታ መግባታቸውን አንስተዋል፡፡
 
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ በዳዋ ዞን የሚገኘው የሑደት የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን ጠቁመው፥ የግንባታ ሒደቱ 70 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
 
በተጨማሪም ላንጋይ የተሰኘው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የግንባታ ሒደት ከ40 በመቶ ማለፉን አስረድተዋል፡፡
 
በክልሉ የከርሰ ምድር ውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የአዋጭነት ጥናት እና የዲዛይን ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
 
ከፍተኛ አቅም ያላቸውን እና በርካታ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ የተባሉት ጉራዳሞሌ እና አዩ የተሰኙ ትላልቅ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችም በቀጣዩ ዓመት የግንባታ ስራቸው እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
 
በሲቲና ፋፈን ዞን አስተዳደሮች በሚገኙ የኤረር እና ቶግ ወቻሌ ከተሞችም ሁለት የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
በሌላ በኩል በክልሉ ድርቅ በሚያጠቃቸው ዞኖች እና ወረዳዎች ላይ የውሃ ጉዳጓድ ቁፋሮ ስራ ጨረታ ወጥቶ ከተቋማት ጋር የስራ ውል መፈረሙን ተናግረዋል፡፡
 
ከሚኒስቴሩ በተጨማሪም በክልሉ መንግስት ወጪ የተከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለመቋቋም በተለያዩ አካባቢዎች የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.