Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ ለፋሲካ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 10፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለፋሲካ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልካም ምኞት መልዕክታቸው “ትንሳኤን ስናስብ ምን ጊዜም በህሊናችን የሚመጣ አንድ ነገር አለ፤ ከህማማት በኋላ ደስታ ከሞት በኋላ ትንሳኤ፤ ከጨለማ በኋላ ብርሃን እንደሚመጣ እናውቃለን” ብለዋል።

ይህ ያለንበት ወቅት የተለየ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ኮሮና ቫይረስ ዓለምን ያለጦር መሳሪያ እንደወረረ እና ሀያላንን ለማንቀጥቀጥ ጊዜ እንዳልፈጀበት ነው ያነሱት።

ይህ ቫይረስ በሀገሪቱ ብዙዎችን መያዙን፣ የሰው ህይወት መቅጠፉን እና በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ሃይማኖታዊ ህይወታችን ላይ ተፅእኖ ማሳደሩን፤ የወረርሽኙ ወደፊት ምን ዓይነት ፈተና እና ችግር ይከተለን በሚል ስጋት የምናስታግደው የስነ ልቦና ተፅእኖም ቀላል አለመሆኑን ተናግረዋል።

“ከገጠመን የበለጠ ፈተና እንዳይገጥመን እንደ መንግስትና እንደ ህዝብ እስከምን ድረስ ራሳችንን ማዘጋጀት እንዳለብን ሁላችንም እንደ አንድ ልብ መክረን እና እጅ ለእጅ ተያይዘን ለተግባራዊነቱ መትጋት ይገባናልም” ብለዋል።

ቫይረሱ ለሚያስከትለው ሀገራዊ ፈተናና ችግር በሚገባ ከተዘጋጀን ያለከባድ ችግር ልንወጣው እንችላለንም ነው ያሉት፥ ፈተናውን የምናልፈው በዝግጅታችን መጠንና ለተግባራዊነቱ ባለን ፅናት ልክ መሆኑን በመጠቆም።

ያለጥርጥር ይህ የወረርሽኝ ጊዜ ያልፋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ማድረግ የሚገባውን ነገር ሁሉ ካደረግን የፈተናውን ጊዜ እናሳጥራለን ብለዋል።

“ከላይ እስከታች በተሰማራንበት መስክ፣ በተሰጠን ሀላፊነት እና ባገኘነው እውቀት የሚገባንን ከሰራን የችግሩ ጊዜ የከፋ ጉዳት ሳያመጣ በአጭሩ ያልፋል፤ የኢትዮጵያ የትንሳኤ ዘመንም ይረዝማል” ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለህክምና ባለሙያዎች ጥበብን፣ ግንባር ቀደም ሆነው ለተሰለፉ ጀግኖች ሀይልና ብርታትን፣ ትግሉን እያገዙ ላሉ ደጋግ ልቦች በረከትን፣ በቫይረሱ ለተያዙት መዳንን፣ በወረርሽኝ ምክንያት ለተጎዱ ፅናትን እና ለህዝቡ ደግሞ መታዘዝን ተመኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.