Fana: At a Speed of Life!

የፍቼ ጨምባላላ በዓል አንድነታችንን በማጠናከር አዲስ ተስፋ የምንሰንቅበት ነው- አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍቼ ጨምባላላ በዓል አንድነታችንን በማጠናከር አዲስ ተስፋ የምንሰንቅበት ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ፡፡

የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፍቼ-ጫምባላላ በዓል በርካታ የበዓሉ ተሳታፊዎች፣ ርዕሳነ መስተዳድሮች የፌዴራል፣ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በተለያዩ ክዋኔዎች ተከብሯል፡፡

በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ÷ የፍቼ ጨምባላላ በዓል አንድነታችንን በማጠናከር አዲስ ተስፋ የምንሰንቅበት ነው ብለዋል፡፡

በዓሉ ለሲዳማ ህዝብ የመልካም ማንነቱ መሰረት የሆኑ በርካታ ዕሴቶችን በውስጡ አካቶ እንደያዘም አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በዓሉን ስናከበር ቂም እና ቁርሾን በመተው ይቅርታና ሰላም እንዲሰፍን በመስራት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

በበዓሉ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ÷ የሲዳማ ህዝብ የጥልቅ ፍልስፍና ባለቤት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መተባበርና መከባበር ለኢትዮጵያውያን ጠቃሚ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ሀገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው÷ በዓሉ የሲዳማን ህዝብ ሰው አክባሪነትና ለወንድማማችነት ያለውን ትልቅ ክብር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ፍቼ ጨምባላላ ያሉ ባህላዊ እሴቶችን በማጠናከር የሰላም ግንባታና አብሮነትን ለማጠናከር መጠቀም ይገባል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.