Fana: At a Speed of Life!

ተማሪዎችን ‘‘ካናዳና እንግሊዝ እወስዳችኋለው’’በሚል ጾታዊ ግንኙነት እንዲፈጽሙ አድርጓል የተባለው ግለሰብ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አራት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በፌስቡክ ማንነቱን ቀይሮ በመተዋወቅ ‘‘ካናዳ እና እንግሊዝ እወስዳችኋለው’’ በማለት ጾታዊ ግንኙነት እንዲፈጽሙ አድርጓል የተባለው ግለሰብ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ።

ግለሰቡ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ እና 20 ግራም ወርቅ ተቀብሎ የማታለል ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ ነው በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ የተወሰነው።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 2ኛ አርቲዲ ወንጀል ችሎት ሲሆን÷ተከሳሹ ታዲዮስ ዘላለም በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ነዋሪ ነው።

ተማሪዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጽ “ናቲ መላኩ” ብሎ ማንነቱን ቀይሮ በካናዳ ነዋሪ በመምሰል ከተዋወቃቸው በኋላ ‘’ካናዳና እንግሊዝ እወስዳችኋለው’’ ብሎ የማታለል ተግባር መፈጸሙ በክሱ ተመላክቷል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሹ ከካናዳ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ በማስመሰል በግንቦትና በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በተለያዩ ቀናቶች ለ4 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የግል ተበዳዮች ስልክ ይደውላል፡፡

በዚህም” ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጉዳይ የሚፈጽምላችሁ ሰው ይመጣል፤ አሻራ የሚወሰደው ከዘር ፈሳሽ እና ከወርቅ ስለሆነ አልጋ ይዛችሁ ጠብቁ በማለት” የግል ተበዳዮች በተለያየ ቀናቶች በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 አልጋ ይዘው እንዲጠብቁ ማድረጉ በክሱ ተጠቅሷል።

አልጋ እንዲይዙ ካደረገ በኋላ ማንነቱን ቀይሮ ወደ አልጋ ቤት በመሄድ የግብረስጋ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ማድረጉም በክሱ ተመላክቷል።

በተጨማሪም ተከሳሹ ከግል ተበዳይ ተማሪዎች ከእያንዳንዳቸው የተለያየ መጠን ያለው በአጠቃላይ 20 ነጥብ 7 ግራም ወርቅ ለአሻራ ምርመራ ያስፈልጋል ብሎ መውሰዱ በክሱ ተገልጿል፡፡

ለጉዳይ ማስፈጸሚያ በሚልም ከእያንዳንዳቸው የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ በአጠቃላይ ግማሽ ሚሊየን ብር በላይ መቀበሉ በክሱ ተዘርዝሯል።

ተከሳሹ ከግል ተበዳዮች መካከል ከአንደኛዋ ተማሪ ጉዳይ ለማስፈጸም “አይፎን “ሞባይል ስልክ ያስፈልጋል በማለት እንድታመጣ በማዘዝ የስልክ ቀፎውን ለመቀበል በቀጠራት ዕለት ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ በኦፕሬሽን ክትትል በቁጥጥር ስር መዋሉ  በክሱ ተመላክቷል።

በዚህም ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 692/1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በማታለል ወንጀል ተደራራቢ አራት ክሶች ቀርቦበታል።

ተከሳሹ ክሱ ከደረሰውና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲል የዕምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር የቦሌ ምድብ ዓቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዳሉ ያላቸውን የግል ተበዳዮችን ጨምሮ 6 ምስክሮችን በችሎት አቅርቦ የምስክርነት ቃላቸውን አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱ የምስክር ቃል መርምሮ ተከሳሹ ወንጀሉን መፈጸሙ በዐቃቤ ሕግ ምስክር ቃል ማረጋገጡን በመግለጽ ተከሳሹ በተከሰሰበት አንቀጽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ነበር።

ይሁንና ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል ባለመቻሉ በመጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በተከሰሰበት በአራት ክሶች በአንቀጽ 692 (1) ስር የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።

ተከሳሹ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረጉን ለህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዢ መፈጸሙን እንዲሁም ለማህበራዊ በጎ አድራጎት  ያበረከተውን አስተዋጾን የሚገልጽ   ከቦሌ ክ/ከ ወረዳ 13  ጽዳት አስተዳደርና ከዚሁ ወረዳ ከሴቶችና ሕጻናት ቢሮ የተሰጠውን ማስረጃ ጨምሮ  አራት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት አቅርቦ በፍርድ ቤቱ ተይዞለታል።

በዐቃቤ ሕግ በኩል ግን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት አለመቅረቡን የችሎቱ ዳኛ ገልጸዋል።

በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሰረት በደረጃ ስድስት በዕርከን 25 መነሻ በ7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነ ሲሆን÷በዕርከን 3 መሰረት ደግሞ በ3 ሺህ ብር የገንዘብ እንዲቀጣ ተወስኗል።

ቅጣቱን የአዲስ አበባ  ማረሚያ ቤት እንዲያስፈጽም የታዘዘ ሲሆን÷የቅጣት ውሳኔ ሲወሰን የግል ተበዳይ ከሆኑት ተማሪዎች መካከል ሁለቱ በችሎት ተገኝተው ቅጣቱን ተከታትለዋል።

በታሪክ አዱኛ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.