ሕዝበ-ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን ይገባል – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1 ሺህ 444ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ምክር ቤቱ በመልዕክቱ÷ ታላቁ የረመዳን ወር ሕዝበ-ሙስሊሙ በፆም በጸሎት የተለያዩ ኃይማኖታዊ ስርዓቶች በማከናወን የሚያሳልፍበት መሆኑን አስታውሷል፡፡
በተጨማሪም ሙስሊሙ ህብረተሰብ ወሩን ለሀገሩና ለወገኖቹ በመፀለይ፣ ላጡ ለተቸገሩ ወገኖች ካለው በማካፈል፣ የተገፉትን በማሰብና ፍቅር በመስጠት የተለያዩ መልካም ምግባራትን በማከናወን ማሳለፉን ጠቁሟል፡፡
ሕዝበ-ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብርም ያጡና የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ፣ በመርዳት እና ማህበራዊና ኃይማኖታዊ ዕሴቶቻችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል ሲል አስገንዝቧል፡፡
ምክር ቤቱ በዓሉ የሠላም፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የመረዳዳት እና የአብሮነት ስሜት ይበልጥ የሚንፀባረቅበት ሆኖ እንዲያልፍም መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡