Fana: At a Speed of Life!

ርዕሳነ መስተዳድሮች ለዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለ1 ሺህ 444ኛው ዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ(ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ÷ዒድ አል ፈጥር ዕዝነት፣ ርህራሄ፣ መተሳሰብ፣ መደጋገፍና አንድነት የሚጠናከርበት ነው ብለዋል።

የረመዳን ፆም ሃይማኖታዊ ሥነ-ምግባርን ጠብቆ የሚፆም ታላቅ ወር በመሆኑ የዒድ-አልፈጥር በዓልን ስናከብርም ሃይማኖታዊ ሕግጋቱ በሚፈቅደው መሰረት ለአካባቢያችን ሰላም በጋራ ዘብ በመቆም ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልፀዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ÷መረዳዳት እና መደጋገፍ ጎልቶ በሚታይበት የረመዳን የጾም ወቅት የታየው መልካም እሴት በቀሪ ጊዜያትም  ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

ባለፉት እድሎች ከመቆጨት ይልቅ ከፊት ለፊት ባለን ብሩህ ተስፋ ላይ ተመስርተን በየተሰማራንበት የስራ መስክ ጠንክረን በመስራት ከድህነታችን ጋር ተጋፍጠን ድል ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙሰጠፌ መሀመድ በበኩላቸው÷ህዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥርን በዓል ሲያከብር በመተዛዘን፣በመተሳሰብ፣በመተጋገዝና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ፆም ወቅት የታየው የመደጋገፍንና መረዳዳት እሴት በማጠናከር እንዲሁም ሰላምንና አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ ማክበር ያስፈልጋልም ብለዋል።

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ለመላው እስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉ  የሰላም፣የጤና፣የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን÷ ህዝበ ሙስሊሙ የመረዳዳትና የአንድነት ወር የሆነውን የረመዳን ወር መልካም ተግባራትን በመፈጸም ማሣለፉን ገልጸዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩም ለሀገር ሠላም የበኩላቸውን ከመወጣት ባለፈ፣ የተቸገሩትን በመደገፍ፣ በመረዳዳት፣ በመተሣሰብ፣ ወንድማማችነትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.