Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ተቋርጦ የቆየውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ተጓዥ ባዛር ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየውን የንግድ እንቅስቃሴ ማስቀጠል የሚያስችል ተጓዥ ባዛር እና የፓናል ውይይት ሊጀምር መሆኑ ተገልጿል።

ተጓዥ ባዛሩ “ሰላም ትግራይ የንግድ እንቅስቃሴ ለቀጠናዊ ሰላም” በሚል መሪ ቃል ነው የሚካሄደው፡፡

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት እንዲሁም የትግራይ ክልል የንግድ ኤጀንሲ በጉዳዩ ላይ በአዲስ አበባ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ÷ዝግጅቱ የተጀመረውን ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እና ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የንግድ እንቅስቃሴው ከመሀል ሀገር ወደ ትግራይ እንዲሁም ከትግራይ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲከናወን የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ባዛሩ እና የፓናል ውይይቱ በመቀሌ ከተማ ተጀምሮ ወደ ውቕሮ፣ ዓዲግራት እና ማይጨው ከተሞች የሚቀጥል መሆኑ ተመላክቷል።

ተጓዥ የንግድ ባዛሩ ሚያዝያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በመቀሌ ከተማ እንደሚከፈትም ጠቁመዋል፡፡
ተጓዥ ባዛር እና የፓናል ውይይቱ ለአንድ ወር የሚቆይ መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

የትግራይ ክልል የንግድ ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ተወካይ አቶ ካሕሳይ ለአከ በበኩላቸው÷ መርሐ ግብሩ በክልሉ ተቋርጦ የቆየውን የንግድ እንቅስቃሴ በጊዜያዊነት እና በቋሚነት ለመቅረፍ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የባዛር እና የፓናል ውይይቱን ማከናወን የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው÷ በመርሐ ግብሩ የመንግስት አካላት እና የግል ተቋማት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በታሪኩ ወ/ሰንበት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.