Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀኔራል ሰዓረ መኮንን ያስገነባውን ሐውልት እና በስማቸው የሰየመውን ፓርክ አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቀድሞው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን ያስገነባውን የመታሰቢያ ሐውልት እና በስማቸው የሰየመውን ፓርክ ዛሬ አስመርቋል፡፡

የመታሰቢያ ሐውልቱ እና ፓርኩ ግንባታ የተከናወነው በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ርዋንዳ አካባቢ ነው፡፡

የምረቃ ሥነ ስርዓቱ የተከናወነው÷ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የጀኔራል ሰዓረ መኮንን ቤተሰቦች እንዲሁም ጀነራል መኮንኖች እና የጀኔራል ሰዓረ የቀድሞ ባልደረቦች በተገኙበት ነው፡፡

ከንቲባ አዳነች በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት÷ ጀነራል ሰዓረ ጀግና ናቸው፤ የሞቱለት ዓላማም ሀገርን ያስቀደመ ነው፡፡

የእርሳቸው ታሪክ ትምህርት ቤት ሆኖ ይቀጥላል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በጀነራል ሰዓረ መኮንን ስም ያስገነባነውን ፓርክ እና የመታሰቢያ ሐውልት ስናስመርቅ ከታሪኩ ቀጣዩ ትውልድ እንዲማርበት በማሰብ ነው ብለዋል።

ጄኔራል ሰዓረ ከልጅነት ጀምሮ ለሰው ልጆች እኩልነትና ፍትሕ በጽናት የታገሉ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት የተጉ፣ “መከላከያ ሠራዊት ሀገር እንጂ ብሔር የለውም” በማለት ለኢትዮጵያ አንድነት የሰሩ ስለመሆናቸውም አንስተዋል፡፡

ወጣቶች ከጄኔራል ሰዓረ የሀገር ፍቅርን፣ በታማኝነት ማገልገልን እንዲሁም ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን ይማራሉ ነው ያሉት ከንቲባ በንግግራቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀኔራል ሰዓረ መኮንን ሐውልት ግንባታ ቦታ ከመስጠት ጀምሮ ለሐውልቱ እና ፓርኩ የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈኑ ተገልጿል፡፡

ጥቁር የታሪክ ጠባሳዎች በፍትሕ አደባባይ እንዲጠራ የጋራ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል ሲሉ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተነሳሽነቱን ወስዶ፣ አስፈላጊውን የማስተባበር ሚናና የበጀት ድጋፍ በማድረግ ይህን የጀግና መታሰቢያ ሐውልት በማስገንባቱ በመከላከያ ሚንስቴር ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ጄኔራል ሰዓረ ከግንቦት 2010 ዓ.ም ሕይወታቸው እስካለፈበት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም በመሆን አገልግለዋል።

በበረከት ተካልኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.