”እንደ ትንሳኤው ብሩህ ቀናችን ላይ እንደምንደርስ እምነቴ ነው”ኢ/ር ታከለ ኡማ
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 10፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለትንሳኤ በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት”እንደ ትንሳኤው ብሩህ ቀናችን ላይ እንደምንደርስ እምነቴ ነው” ብለዋል፡፡
“ምንም እንግልት፣ ምንም ስቃይ፣ ምንም መከራ ዘላለማዊ አይደለም” ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ ።
ምክትል ከንቲባው “በመውደቅ መነሳት፣ በፆምና በስግደት፣ በጥሞናና ፀሎት የተጋችሁበት ወራት ወደ ደስታና እረፍት እንደሚያመጣን ምኞቴም እምነቴም ነው” ብለዋል።
ምን ብዙ ብንደክም፣ ምን ሀዘን ቢገባን፣ አለመፅናናትን ግን አንችልምና ምን ብንፈትን መንገላታታችን ቢበረታ፣ ከመከራችን ተስፋችን ከድህነታችን ፍቅራችን ይበልጣልና የተጋርጠብንን ከባድ ፈተና አሽንፈን እንደ ትንሳኤው ብሩህ ቀናችን ላይ እንደምንደርስም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
“ትንሳኤ ከመንፈሳዊ ሀሳቡ ባለፈ ለምድራዊ ህይወታችንም ጉልበት ሰጪ ነው፤ ትንሳኤ ለእውነትና እምነት ዋጋ የመክፈል ምልክት ነው፤ ትንሳኤ ለሌሎች ህይወት ዋጋ እስከ ህይወት ድረስ የመክፈል ማሳያ ነው” ብለዋል።
ሀገራችን ከዛ አልፎ ዓለማችን አሁን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ መጥፎ የሚመስል ነገር ግን ደግሞ እንደ ህዝብ ያለን ጥንካሬ የሚለካበት መተሳሰባችንና መተባባራችን በጋራ የሚያቆመን ብርቱ ምሶሶ የሆነበት ወቅት ላይ ነው የምንገኘው።
በመተሰሳሰብ ስንራመድ ለሌሎች ማሰባችን በተግባር ሲገለጥ ይህ ጊዜ አልፎ ትንሳኤ ይመጣል” ማለታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።