በጋምቤላ ከተማ የ8 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ስምንት ኪሎ ሜትር የሸፈነ 9ኛው ዙር የ”ፋን ኢትዮጵያ የጎዳና ላይ ሩጫ” በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመምርጥና ለማብቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በውድድሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ጁል ናንጋል÷ ስፖርት የሰላምና የአንድነት መገለጫ ነው ብለዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ እንድትል አትሌቶች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
“የአርአያዎቻቸውን ፈለግ ተከትለው ሀገርን በዓለም አደባባይ የሚያኮሩ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት በሁሉም ዘርፍ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል።
የፋን ኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስኪያጅ አትሌት ፋንቱ ሜጌሶ በበኩላቸው÷ ስፖርት ለጤንነትና ለአካል ብቃት ካለው ጠቀሜታ በተጨማሪ የወንድማማችነትና የአንድነት እሴቶችን በማጠናከር ረገድ የጎላ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመምርጥና ለማብቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም መገለጹን ከክልሉ ኮሚኒኬሽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡