በመንግስት ጤና ተቋማት ዲጅታላይዝ የመድሃኒት ስርጭት አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና የከነማ መድሃኒት ቤቶች ዲጅታላይዝ የመዲሃኒት ስርጭት አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታውቋል።
የአገልግሎቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ንጉሴ÷መድሃኒትን ከሀገር ውስጥና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ገዝቶ በማከማቸት የማሰራጨትና ተደራሽ የማድረግ ስራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ቢሆንም መድሃኒቶች መጋዘን ውስጥ እያሉ አልፎ አልፎ እጥረቶች የሚከሰቱበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የመድሃኒት ግዢ ዲጅታል መደረጉ የመድሐኒት እጥረትን በማቃለልና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
የመድሃኒት ግዢና ስርጭት በማንዋል በነበረበት ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ እስከ 200 ቀናት ይፈጅ እንደነበር አስታውሰው÷ ዲጅታል ከተደረገ በኋላ ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎትን ጨምሮ በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና የከነማ መድሃኒት ቤቶችን በዲጂታል የመድሃኒት ግዢና ስርጭት መተግበሪያ ማስተሳሰር ተችሏል ብለዋል።
የመድሃኒት ክምችትና የስርጭትን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች የሚቀጥሉ መሆኑን ጠቅሰው÷ አጋር አካላትም የሚሳተፉበት ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጤና ተቋማት የመድሃኒት ክምችታቸውን በቀላሉ ለማወቅ የሚችሉበት የአሰራር ስርዓት እውን እንደሆነ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጤና ፕሮግራም የሚካተቱ መድሃኒቶችን ከክፍያ ነጻ በማድረግ ለተጠቃሚዎች በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችም ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
በጤና ፕሮግራም የሚካተቱ መድሃኒቶችን በማቅረብ ከ95 በመቶ በላይ የተሳካ ስራ መከናወኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።