Fana: At a Speed of Life!

ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያን የመልሶ ማቋቋም ስራ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያን የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ገለፁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ጋር በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ላይ ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ÷ የሰላም ስምምነቱ በተገቢው መንገድ እንዲሄድ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት እና ነዋሪዎችን ለማቋቋም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ሚኒስትሯ በበኩላቸው ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ የሰላም ሂደት አካል በመሆኗ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልፀዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡

ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካ መፍትሄዎች በመስጠት ግጭቶችን ከመፍታት ባለፈ በመልሶ ግንባታ እና መልሶ ማቋቋም ስራዎች ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋም ስራዎችን በተለይም በትምህርት ዘርፍ ላይ ለማገዝ ፍላጎት እንዳላት መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.