Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተለያየ መስክ ውጤት መመዝገቡን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በልማትና በፖለቲካ መስኮች ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የኦሮሚያ ክልል የሦስተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

አቶ ሽመልስ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ መድረኩ ያሉብን ክፍተቶችና ስኬቶችን በመለየት ለመጪው የበጀት ዓመት የልማት ዕቅድ አፈፃፀም የሚበጀንን መሰረት የምናስቀምጥበት ነው ብለዋል፡፡

የክልሉን ሕዝብ የኢኮኖሚ ልማት ንቅናቄ አካል የማድረግ ሥራ፣ በመንግሥት የተቀረጹ የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ውጤታማነትና የአመራሮች ተልዕኮን የመወጣት ብቃት እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ባለው መዋቅር መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

የዜግነት አገልግሎትና የባህል ፍርድ ቤቶች ለሕዝቡ ያስገኙትን ውጤት በመገምገም ቀጣይ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል መንግስት በቅርቡ የሚካሄደው የሰላም ድርድር የተሳካ እንዲሆን እና የሕዝቡ ሰላማዊ ኑሮ እንዲቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት አለው ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፡፡

ስለሆነም ለሰላም ድርድሩ ስኬት ሁሉም አካላት የክልሉን ሕዝብ ጥቅም በማስቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ጠይቀዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ለውይይቱ ፍሬያማነት የክልሉ ሕዝብ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሁም የተለያዩ ድርጅቶች እና አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ጥረት ያደረጉ እና እያደረጉ ያሉ አካላትንም አቶ ሽመልስ አመስግነዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግጭት ተቋጭቶ የሰላም አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት በማድረጋቸው ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ÷ መድረኩ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ከመታገል አንፃር የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክረን ለማስቀጠል የሚያስችል ነው ብለዋል።

የተንጠባጠቡ ሥራዎችን በመለየት በቀጣይ ቀሪ ወራት መፈፀም የሚቻልበት የጋራ አቅጣጫ ይቀመጣል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተለይም ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ማስወገድ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.