Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል መንግስት ተቋማት የ2016 በጀት ስሚ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በየዓመቱ የበጀት የጊዜ ዑደቱን ጠብቆ የሚደረገው የበጀት ስሚ ፕሮግራም የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማትን የ2016 በጀት በመስማት ተጀምሯል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ፕሮግራሙን ባስጀመሩበት ጊዜ እንደገለጹት÷ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የመደበኛና የካፒታል በጀታቸውን በተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ መሰረት ማቅረብ አለባቸው፡፡

የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚመደብላቸውን በጀት በአግባቡና በቁጠባ የመጠቀም ሃላፊነት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የ2016 በጀቱን ያቀረበው የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በውጭ ሀገራት ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑ ተነስቷል፡፡

በሀገር ውስጥም ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት የገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚደግፍም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በ2016 በጀት ዓመት በሂደት ላይ ያሉ የካፒታል ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር በተጨማሪም የባህልና ስፖርት፣ የገቢዎች ሚኒስትርና ተጠሪ ተቋማት የ2016 በጀት ዝግጅታቸውን ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.