የሀገር ውስጥ ዜና

በፒራሚድ ንግድ ስልት ላይ የተሰማሩ ሁለት ኩባንያዎች በህግ ሊጠየቁ ነው 

By Mikias Ayele

April 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፒራሚድ ንግድ ስልት ላይ የተሰማሩ ሁለት ኩባንያዎችን በህግ ለመጠየቅ ሂደቶች መጀመሩን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፒራሚድ ንግድ ስልት የሚያስከትለውን ማህበራዊ ምስቅልቅል ለማስቆም አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለምን የፒራሚድ ንግድን ማስቆም አልተቻለም ሲል ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን ጠይቋል።

በሚኒስቴሩ የሸማቾች ጥበቃ ባለሙያው አወቀ ግዛው ከፍተኛ መደለያዎችንና በአቋራጭ ትከብራላችሁ የሚል አደናጋሪ መልዕክትን በማስተላለፍ ህገወጡን የንግድ ስልት ተግብረው ብዙዎችን የጎዱ ድርጅቶች ዛሬም መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

ችግሩ በርካቶችን ለማህበራዊ ቀውስ መዳረጉን በመጥቀስም እልባት እንደሚያስፈልገው ነው የሚገልጹት።

መፍትሄው የብዙ ባለድርሻዎችን ስራ የሚጠይቅ ነው ያሉት አቶ አወቀ በቂ ትኩረት ግን እንዳላገኘ ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል ቀጥተኛ ንግድ የሚመራበት መመሪያ አለመኖሩንና በፒራሚዳዊ ስልት የተሰማሩ ድርጅቶች ሲደረስባቸው የህግ ክፍተቱን እንደሽፋን እንደሚጠቀሙበት አንስተዋል።