Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ዛሬ ባሳላፈው ውሳኔ አረጋገጠ፡፡

ምክር ቤቱ የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የተደረሰውን ሥምምነት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍም አመላክቷል፡፡

በመግለጫው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ቀጣና ለአውሮፓ ኅብረት ቁልፍ ስትራቴጂያዊ አጋር መሆኗን አንስቷል፡፡

በመሆኑም የአውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ የምታደርጋቸውን ጥረቶች እና መሻሻሎች አድንቆ በሚያስፈልገው ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑንም አፅንዖት ሰጥቷል።

የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚፈልግ እና ግንኙነቱን ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለማሳደግ እንደሚሠራም ጠቁሟል።

በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉ ውጥረቶች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ጉዳይ በትኩረት እየተከታተለ መሆኑን በማንሳት፥ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ጥረት እንደሚያደርግም ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.