Fana: At a Speed of Life!

የሀገራዊ ሽግግር ፍትሕ ምክክር መድረክ በተለያዩ የክልል ከተሞች መካሄድ ጀምሯል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሎች ደረጃ የሚካሄደው የሽግግር ፍትህ ምክክር መድረክ በ58 ከተሞች ከሚያዝያ እስከ ነሃሴ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ ሲስተዋሉ ከቆዩ መጠነ-ሰፊ እና ውስብስብ በደሎች፣ ፈተናዎችና ግጭቶች በመነሳት ሙሉ ፍትህ የሚሰጥበትን መንገድ ለመዘርጋትና ማህበረሰቡ ወደቀደመ ሁኔታው እንዳይመለስ ለማድረግ የሚያስችል ዘላቂ ሰላም፣ እርቅና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መገንባት ፍፁም አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ብሏል።

ከዚህ በመነሳትም የኢትዮጵያ መንግስት የሽግግር ፍትህ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ ለሀገር ሠላም፣ ዲሞክራሲና ዕድገት ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን በመገንዘብ ሂደቱን በተሟላና በተቀናጀ መልኩ ለመተግበር የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱም አንስቷል።

በዚህ ረገድ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማርቀቅ ስራ ለመጀመር የሚያስችለው የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጮች መነሻ ሰነድ የፍትሕ ሚኒስቴር ባደራጀው ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን መጠናቀቁን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ለሀገራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት የሚያስፈልገው ብሄራዊ ምክክር የማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም መከናወኑ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ በክልሎች ደረጃ የሚካሄደው ምክክር በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 58 ከተሞች ከሚያዝያ እስከ ነሃሴ 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለማከናወን መርሐ ግብር መውጣቱን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።

የመጀመሪያ ምዕራፍ መድረክ በቅርቡ በአዳማ ከተማ መካሄዱን ጠቁሞ ÷በዚህም ፍጹም ነፃ እና ገለልተኛ በሆነ ሂደት የተጋበዙ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች የሚወክሉ ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ ንቃት እና የባለቤትነት ስሜት መሳተፋቸው ተነስቷል፡፡

በባለሙያዎች በቀረቡ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ክርክር መካሄዱን ፍትህ ሚኒስቴር በመግለጫው ያነሳ ሲሆን ፥ ጠቃሚ ነው ብለው የሚያስቧቸውን ምክረ ሃሳቦችን ማቅረባቸው ተጠቁሟል።

የፖሊሲ አማራጭ ሰነዱን ለማዳበር የሚያስችል ሰፊ ግብዓት የማሰባሰብ ስራም ተከናውኗል ነው የተባለው።

መድረኩ በቀጣይ ሁለት ሣምንታት በ15 የተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንደሚካሄድም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.