143 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አሳይተዋል – ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 143 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።
በዚህም በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከሀገር ውስጥ 18 ቢሊየን ብር ከውጭ ደግሞ 125 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
በኮቪድ-19 እና በዓለም የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት የባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍላጎት ተቀዛቅዞ መቆየቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ፥ አሁን ላይ ጥሩ መሻሻሎች መታየታቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 67 አዳዲስ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሃገር ውስጥ መጥተው መዋዕለ- ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለመሰማራት ሰፊ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 143 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ነው ሚኒስትሩ የጠቀሱት።
በዘርፉ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪን ለማበረታታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ÷ ግንባታቸው ተጠናቆ ባለሃብቶች ሳይገቡባቸው የቆዩ ኢንዱስትሪዎች እንደነበሩም አንስተዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ በተደረገው ጥረት 332 ባለሃብቶች ወደ ሥራ ለመግባት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል እስካሁን 67 የሚሆኑት ስምምነት የተፈረመባቸው ሲሆን÷ 16ቱ ወደ ግንባታ መግባታቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ 25ቱ ፋብሪካዎቻቸውን ሲያቋቁሙ ስምንቱ ደግሞ ወደ ማምረት ገብተዋል ብለዋል።