Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ በእነ ዶክተር ወንድወሰን አሰፋ ላይ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጊዜ ወንጀል ችሎት ዶክተር ወንድወሰን አሰፋ፣ ዶክተር መሠረት ቀለመወርቅ እና ገነት አስማማው የተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ፓሊስ ያቀረበውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የፌዴራል ሥርዓቱን ኢ- ህገ መንግስታዊ በሆነ አግባብ በሀይል እርምጃ ለመቀየር በማቀድ ባዘጋጁት ስትራቴጂካዊ ሰነድ በመመራት በወታደራዊ ሥልጠና ክንፍ የፖለቲካ ክንፍ፣ በሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ክንፍ እና ሌሎች የድርጊት መርሃ ግብር አፈጻጸምን በማውጣት መዋቅራቸውን በመዘርጋት፣ የሥራ ስምሪትና ክፍፍል በማድረግ፣ በህቡዕ ገንዘብ በማሰባሰብና በመመደብ፣ ታጣቂ ሃይል በማሰልጠንና በማደራጀት፣ በማስታጠቅ እንዲሁም በትጥቅ የታገዘ ህዝባዊ አመፅን በመቀስቀስ፣ የሥራ ማቆም አድማን በመቀስቀስ እንዲሁም የፋይናንስ ገቢ ለማግኘት ህገወጥ የፋይናንስ ሰንሰለትን እስከ ውጪ ድረስ በመዘርጋት ለሽብር ተግባር ገቢ ሲያሰባስቡና ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በተቀናጀ መልኩ ለሽብር ስራ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው ብሎ መጠርጠሩን የምርመራ መነሻ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

ተጠርጣሪዎች ዓለማቸውን ለማሳካት እንዲያመቻቸው በማቀድ ተቻችሎና ተፋቅሮ በሚኖረው ህብረተሰብ መካከል እርስ በርስ መጠላላትንና መጠራጠርን በመንዛትና በመቀስቀስ አንዱን ህዝብ በሌላ ህዝብ ላይ እንዲነሳ በተደራጀ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል ሲል መርማሪ ፖለስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል፡፡

በዚህ ህገ ወጥ እንቅስቃሴያቸው ምክንያት የበርካታ ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ፣ የህዝብና የመንግስት ንብረቶች እንዲወድሙ፣ የማህበራዊ አገልግሎት እንዲቋረጥ፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲቆምና በየጊዜው እንዲስተጓጎል፣ የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ አመጽን በመቀስቀስ የሽብር ድርጊት ወንጀልን በመፈጸም በንጹሐን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ሲል መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ለዚህም 14 የምርመራ ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ያቀረበው አቤቱታ ሊያስጠረጥር የሚችል የወንጀል መነሻ የለውም በማለት የምርመራ ቀጠሮ ውድቅ ተደርጐ የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲከበር ተከራክረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ድርጊት ውስብስብ እና የሀገርን አንድነት የሚያፈርስ፣ በህዝብ መካከል መተማመን እንዳይኖር፣ ዜጎች በሠላም ወጥተው እንዳይገቡ፣ በአገሪቱ ሥርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን ለማድረግ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ለሽብር ተግባር ሲንቀሳቀሱ የነበሩና በርካታ ሥውር የአገር ማፍረስ ሴራዎች ያሉበት ነው ብሎ ፖሊስ ተከራክሯል።

ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ከአገር ሊሸሹና ሌሎች ማስረጃዎችንም በማሽሽ ምርመራውን ሊያደናቅፉ የሚችሉ መሆናቸው ታምኖበት የምርመራ ስራውን በስፋት በሰውና በሰነድ ማስረጃ አጣርቶ ለሚመለከተው የፍትህ አካል ማቅረብ እንዲቻል የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ የጊዜ ቀጥሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ክርክሩን የተከታተለው የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጐ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀናት የምርመራ ማጣሪያ የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.