የሸዋል ዒድ በዓል ከነገ ጀምሮ በሐረሪ ክልል ይከበራል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሸዋል ዒድ በዓል “ሸዋሊድ ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለአብሮነት እና ለቱሪዝም ዕድገት” በሚል መሪ ሐሳብ ከነገ ጀምሮ በሐረሪ ክልል መከበር እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡
ክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ተወለዳ አብዶሽ በሰጡት መግለጫ÷ በዘንድሮ የሸዋል ዒድ በዓል የሐረሪን ሕዝብ ዕሴት ከማስተዋወቅ ባለፈ የቱሪዝንም መዳረሻዎችን እና ባህልን ለማስተዋወቅ ይሰራል ብለዋል፡፡
የዓሉ ዋዜማም በዋናነት በ “አው አብቀራ” እና “አው ሹሉም አህመድ” በሮች እንደሚከበር ነው የጠቆሙት፡፡
በበዓሉ ÷ የክልሎች ባህላዊ ፌስቲቫል፣ ትርዒት፣ የእውቅና መርሐግብር፣ የጀጎል አዋርድ፣ የቅርስ ዕድሳት ሥራ ማስጀመሪያ እንዲሁም የሐረሪ እና የአባገዳዎች ባህላዊ ቤቶች ይመረቃሉ ነው ያሉት፡፡
የሐረሪ ሕዝቦች በሂጅራ የዘመን አቆጣጠር በሸዋል ወር ሥድስቱ የሱና ጾም ከተጾመ በኋላ የሚያከብሩት የሸዋል ዒድ በዓል ባህላዊ ዕሴታቸውን የሚገልጹበትን ነው፡፡
በመራኦል ከድር