የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ምዝገባ ተጀመረ

By Alemayehu Geremew

April 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል መደበኛ ትምህርት ለመጀመር የሚያስችል ምዝገባ በሁሉም ትምህርት ቤቶች መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በዛሬው ዕለትም ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል የደረሱ ተማሪዎች ሲመዘገቡ መዋላቸውን የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዳኘው አይጠገብ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም መደበኛ ትምህርት በክልሉ እንደሚጀመርም ነው የገለጹት፡፡

በግጭት ወቅት ለባከነው የትምህርት ጊዜ ማካካሻ  እንደሚሰጥ አመላክተዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ከአካባቢያቸው ርቀው የቆዩትን ለመመለስ እንዲሁም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ ትምህርት ለማስጀመር እንዲቻል ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከግብረ ሠናይ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት ሲሠሩ መቆየታቸው አስታውሰዋል፡፡

በኮሮና ቫይረስ እና በነበረው ግጭት ምክንያት ለ ሰባት ሴሚስተር ትምህርት ሳይሰጥ መቆየቱንም ነው ያመላከቱት፡፡

በአፈወርቅ እያዩ