Fana: At a Speed of Life!

ወደ ትግራይ ተቋርጦ የነበረው የየብስ ትራንስፖርት ዳግም ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የየብስ ትራንስፖርት ዳግም መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከአማራ፣አፋርና ትግራይ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በሰጠው መግለጫ÷ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በተሰራው በርካታ ስራ ወደ ትግራይ ክልል የሚደረግ የየብስ ትራንስፖርት መጀመሩ ተመላክቷል፡፡

በዚህም የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት መሠረት ከሚያዝያ 14 ቀን 2015ዓ.ም ጀምሮ በተደረገው የሙከራ ትግበራ ከአዲስ አበባ ትግራይ ክልል እንዲሁም ከትግራይ ክልል ወደ አዲስ አበባ እስካሁን በተለያዩ አቅጣጫዎች 19 አውቶብሶች መመላለሳቸው ተነግሯል።

የየብስ ትራንስፖርት መጀመሩ በህብረተሰቡ በኩል ከፍተኛ ደስታ መፍጠሩንና ለትራንስፖርት ጉዞው መሳካትም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተገልጿል።

በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ ህገወጥ ኬላዎችን በማስወገድና ቁጥጥሩን በማጥበቅ ረገድም የአካባቢው ባለስልጣናትና አመራሮች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።

የደህንነት ቁጥጥር በማድረግ አጠቃላይ የትራንስፖርት መስመሩን የፌደራል ፖሊስ ይቆጣጠረዋል ነው የተባለው።

በዓለምሰገድ አሳዬና ሰለሞን ይታየው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.