Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች የመልሶ ማቋቋም ስራን በማጠናከር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተሰራ ነው-  አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስትና ብልፅግና ፓርቲ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን በማጠናከር የተሻለች ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ፋራህ በመቀሌ ለልዑካን ቡድኑ ለተደረገው ኢትዮጵያዊ ስሜት የታየበት ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።

የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር  ለረጅም ዘመናት መታገሉን ገልጸው÷ ኢትዮጵያውያን መፃኢ እድላቸው እጅግ የተቆራኘ መሆኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት በተሟላ መልኩ የሚሳካው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ወንድማማችነቱን አጥብቆ በጋራ መስራት ሲቻል ነው ብለዋል።

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከንቲባዎች ጉብኝትም ሰላምን የማፅናት አብሮነትን በተግባር የመግለጥ ጉዞ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት የኢትዮጵያ ህዝብ የተጎዱ አካባቢዎችን በጋራ ለመገንባት ያለውን ዝግጁነት የሚገልጽ ነው ብለዋል።

መንግሥት የጀመረውን ጥረት ይበልጥ በማጠናከር ሁሉንም አቅሞች አጠናክሮ ህዝቡን ከደረሰበት ጉዳት ለማውጣት በትጋት መስራቱን ይቀጥላልም ነው ያሉት።

ለዚህም በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያንና አጋር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው÷ ልዑኩ ትግራይ ክልል በመገኘት በጦርነቱ የተከሰተውን ጉዳት ጎብኝቶ አጋርነቱን ስላረጋገጠ እናመሰግናለን ብለዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ ለሚሰራቸው ስራዎች የዛሬው ጉብኝት ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው÷ የመልሶ ግንባታ ስራውን ለማፋጠንና ሰላምን አጠናክሮ ለመቀጠል በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.