Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች የ5 ሚሊየን ብር የዓይነት ድጋፍ አድርጓል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ድጋፉን ሲረከቡ እንደተናገሩት ፥ በከተማው በግለሰብ ቤት ተጠግተው የሚኖሩት ሳይጨምር በመጠለያ ጣቢያ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡

በዚህም የምግብ፣ የመጠለያና የአልባሳት ችግሩ ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡

በተለይም ህፃናት፣ አቅመ ደካሞችና ሴቶች በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም ሁለት ሄክታር በማይሞላ ቦታ ውስጥ እስከ 12 ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃዮች ተጨናንቀው ለመኖር መገደዳቸውን ከንቲባው አስረድተዋል፡፡

ሁኔታዎች ተስተካክለው በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ ሌሎች አካላትም ሆኑ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ፈቱዲን ሀጂ ዘይኑ በበኩላቸው ፥ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ተባብረው ድጋፉን ማሰባሰባቸውን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከችግራቸው እስኪወጡ ድረስም የሃይማኖት ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ የሚመለከታቸው አካላትና ሁሉም ሰው ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህ ሥራ የተሳተፉ የአዲስ አበባ እና በሀገሪቱ የሚገኙ የሙስሊም ማኅበረሰብ እንዲሁም ያስተባበሩ አካላትን ማመስገናቸውን ከደብረብርሃን ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.