Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል መንግስት በአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ኃዘን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል መንግስት የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ኃዘን ገለጸ፡፡

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

በዛሬው ዕለት ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የተከበሩ አቶ ግርማ የሺጥላ እና የግል ጥበቃዎቻቸው ላይ የመንግሥትና የድርጅት ሥራዎችን በሰሜን ሸዋ ዞን ሠርተው ከመሀል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሀን ሲመለሱ ልዩ ቦታው መንዝ ጓሳ አካባቢ በታጠቁ ፅንፈኛ ሃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በደረሰው ልብ ሰባሪ ጥቃት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰማውን መሪር ሀዘን ይገልጻል፡፡ እነዚህ ፅንፈኛ ሀይሎች በሀሳብ ትግል ማሽነፍ ያልቻሉትን በኀይል ለማስፈፀም ያደረሱት ጥቃት ዓላማውን ማሳካት የማይችልና ጊዜው ያለፈበት፣ ዘመኑን ያልዋጀ የጥፋት መንገድ ስለሆነ አምርረን የምንታገለው ተግባር ነው፡፡

እነዚህ ፅንፈኛ ሃይሎች በክልሉ ውስጥ የሚፈጽሙትን ስርዓት አልበኝነትና የሽብር ድርጊት ለመከላከል፤ ለመቆጣጠርና ሕግ ለማስከበር የክልሉ መንግሥት እርምጃ ይወስዳል:: የጥቃቱን አድራሾችም ለሕግ ያቀርባል፡፡ ማንኛውም በጥቃቱ የተሳተፉ ሃይሎችንንና ተባባሪዎችን ሁሉ ከያሉበት ለሕግ በማቅረብ አስፈላጊው ፍትሕ እዲረጋገጥ ይደረጋል፡፡

መላው የክልላችን ሕዝብ የተፈጠረውን የሽብር ድርጊት ከማውገዝ ጀምሮ ወንጀለኞች ለሕግ ቀርበው ፍትህ እንዲረጋገጥ፣ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግና እንዲረጋጋ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የጥፋት ኃይሎች ከዚህ በላይ ዓላማ ያላቸው እና ክልሉን የማፍረስ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ በኋላ የክልሉ መንግሥት እንደማይታገስ እና ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ እናረጋግጣለን፡፡

የክልሉ መንግሥት ለቤተሰቦቻቸው፤ ወዳጆቻቸው፤ ለስራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የክልላችን ሕዝብ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልጻል፡፡ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያሳርፍልን!

እንዲሁም የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል።

የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በሀዘን መግለጫው ÷ አቶ ግርማ ለኢትዮጵያና ለአማራ ክልል ህዝቦች ወንድማማችነት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ አመራር ሲሰጥ የነበረ ባለ ምጡቅ አዕምሮ፣ አንደበተ ርዕቱ፣ በሳል የፖለቲካ አቅምና ተሻጋሪ እይታ የነበረው ድንቅ የሀገር ልጅ ነው ብሏል፡፡

በደረሰው ልብ ሰባሪ ጥቃት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የተሰማውን ሀዘን የገለጸ ሲሆን ÷ ያልተገባ ፍላጎትን በጉልበት ማስፈፀም የማይቻልና ጊዜው ያለፈበት ዘመኑን ያልዋጀ የጥፋት መንገድ ስለሆነ አምርረን የምንታገለው ተግባር ነው ሲልም ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.