Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በአማራ ክልል ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በሃዘን መግለጫቸው÷ “ወንድማችን አቶ ግርማ የሺጥላ በስራ ላይ እያለ በታጠቁ ኃይሎች ግድያ ተፈጽሞበታል፤ እንዲህ አይነት እብሪተኝነት ውድቀትን እንጅ ድልን አያጎናጽፍም፤ ጥፋትን እንጅ ሰላምን አይሰጥም” ብለዋል፡፡

የህዝባችን የቆየ መገለጫው ስርዓታዊነት፣ ፍትሃዊነትና እኩልነት ነው፤ ከዚህ ታሪኩና ስነልቦናው ጋር የሚቃረኑ ተግባሮች በሙሉ ስርዓት አልበኝነት የወለዳቸው ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

በህግና ስርዓት እንጅ በደቦ ፍርድ የግልም ሆነ የቡድን፤ እንዲሁም የህዝብም ሆነ የአገር ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት አይቻልም፤ምክንያቱም የስርዓት አልበኝነት የመጨረሻ መዳረሻው ጥፋትና መጠፋፋት ነው ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ ዘላቂ ሰላሙን ለማረጋገጥ አንዲህ አይነት ስርዓት አልበኝነትንና ህገወጥ ተግባሮችን ከመንግሥት ጎን ቆሞ ሊያወግዝና ሊታገል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ለአማራ ክልል ሕዝብ፣ ለሟች ለቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶችም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.