በመዲናዋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላዎችን በተላለፉ 268 አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላዎችን በተላለፉ 268 አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ።
የመምሪያው የትራፊክ ሙያ የህዝብ ግንዛቤ ማሳደጊያ ዲቪዚዮን ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሠለሞን አዳነ፥ 195 አሽከርካሪዎች ትርፍ ሰው በመጫን እና 73 አሽከርካሪዎች ደግሞ ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ በማስከፈል እርምጃ እንደተወሰደባቸው ገልፀዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን በመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ታስቦ በተለይም የትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ቀደም ሲል ከሚጭኑት የተሳፋሪ ቁጥር በግማሽ መቀነስ እንዳለባቸው በአዋጁ ግዴታ ቢጣልባቸውም አንዳንዶች ክልከላውን ተላልፈው መገኘታቸው ተገልጿል።
በተመሳሳይ ተሳፋሪውን ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ የተገኙ አሽከርካሪዎች መኖራቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላ የተደረገባቸው ተሽከርካሪዎች ቀደም ሲል ይጭኑ ከነበረው የተሳፋሪዎች ቁጥር 50 በመቶ እንዲጭኑ መመሪያ መተላለፉ ይታወሳል።
አሽከርካሪዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገጉ ክልከላዎችን በማክበር ተባባሪ እንዲሆኑ ኃላፊው መጠየቃቸውንም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision