Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በተሻለ መሠረት ላይ እያጸናች ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በተሻለ መሠረት ላይ እያጸናች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በታንዛንያ፣ ኮሞሮስ፣ ቡሩንዲና ኡጋንዳ ያደረጉት ጉብኝት አፍሪካዊ ወዳጅነትን ለማጠናከር ማስቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገልጸዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ አፍሪካ የኢትዮጵያ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ትኩረት እና የዲፕሎማሲ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
ጉብኝቱ አፍሪካውያን ወዳጆቻችንን የማጽናትና የማስፋት ዲፕሎማሲያዊ አካል ጥረት መሆኑን ተናግረዋል።
ከታላቁ የህዳሴ ግድብና የናይል ተፋሰስ አንፃር የበለጠ ለመደጋገፍ እና መግባባት እንዲደረስ ማስቻሉን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በኩል የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር እንዲቀጥል በጉብኝቱ ወቅት በተደረጉ ውይይቶች ከመግባባት ላይ መደረሱንም አንስተዋል።
አምባሳደር መለስ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እየተሳተፉበት ያለው የኢንቨስትመንት ጉባኤ ሀገሪቱ የሰላም ስምምነቱን እያጸናች ልዩ ትኩረት ወደ ምትሰጠው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ፊቷን እያዞረች ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ጦር ኃይሎች መሪ ጄኔራል አብደልፈታህ አልቡርሃን እና ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ጋር በስልክ መወያየታቸውንም ገልፀዋል።
በዚህም የሱዳን ችግር በሰላም እና ሱዳን መራሽ በሆነ አካሄድ ብቻ መፍትሄ ማግኘት እንዳለበት መነጋገራቸውን ኢትዮጵያም ለዚሁ እንደምትሰራ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
በሱዳን ለዜጎች ሊደረግ የሚችለው ድጋፍም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ያሉት አምባሳደር መለስ ሱዳን ካጋጠማት ወቅታዊ ፈተና እንድትወጣ ኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታ ከሱዳናዊያን ጎን መሆኗን ገልጸዋል።
በሃብታሙ ተ/ስላሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.