Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ በቀጣዩ ሣምንት ባለድርሻ አካላትን ተሳታፊ ማድረግ የሚያስችል ልየታ ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚቀጥለው ሳምንት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ማድረግ የሚያስችል የተሳታፊ ልየታ ስራ በወረዳ ደረጃ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) እንዳሉት ከሚቀጥለው ሣምንት ጀምሮ ለምክክር ሂደቱ ወሳኝ የሆነው የተሳታፊ ልየታ መካሄድ ይጀምራል፡፡

ሁሉንም አይነት የሕብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ ማድረግ የሚያስችል የልየታ ስራ እንደሚከናወንም ነው ዋና ኮሚሽነሩ ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

በሂደቱ በእያንዳንዱ ወረዳ ዘጠኝ ባለድርሻ አካላት እንደሚኖሩ እና እያንዳንዳቸው 50 ተወካዮቻቸውንእንደሚመርጡ አብራርተዋል፡፡

እነዚህ አካላት ከተወያዩ በኋላ የውይይት ጽንሰ ሐሳብንና አጀንዳ አሰባሰብን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከዘጠኙም ባለድርሻዎች ሁለት ሁለት ተወካዮች ተመርጠው ወደ ክልል የሚሄዱበት አሰራር መቀመጡን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ከእያንዳንዱ ወረዳ የተወከሉ 18 ሰዎች ወደ ክልል በመሄድ ባመጧቸው አጀንዳዎች ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ የሚመረጡ አጀንዳዎችን ወደ ኮሚሽኑ እንደሚልኩ ነው ያመላከቱት፡፡

በተጨማሪም በክልል ደረጃ ከተደራጁ የሕብረተሰብ ተወካዮች ማለትም ከሠራተኛ ማኅበራት፣ ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎችም አደረጃጀቶች አጀንዳዎች የሚሰበሰቡ ይሆናል ብለዋል፡፡

በፌደራል ደረጃም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎችን የማሰብሰብ ሥራ በሂደት እንደሚሠራ ነው የገለጹት፡፡

በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ዜጎችም በሚዘረጋላቸው የመረጃ ግንኙነት አውታር አጀንዳ እንዲያቀርቡ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

አጀንዳዎች ከተሰበሰቡ በኋላ በፌደራል ደረጃ አገራዊ የምክክር መድረክ የሚዘጋጅ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ኢትዮጵያውያን በዝርዝር እንዲመክሩ ይደረጋል ነው ያሉት።

ኮሚሽኑ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የጋራ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የተቋቋመ በመሆኑ ለዚህ ዓላማ መሳካት ሁሉም ተሳትፎውን እንዲያጠናከር ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.