የሀገር ውስጥ ዜና

የነዳጅ እጥረት እንዳለ የሚያስመስሉ ማደያዎች ከነዳጅ ሥርጭት ይታገዳሉ

By Alemayehu Geremew

April 28, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ነዳጅ በመደበቅ የነዳጅ እጥረት የተፈጠረ አስመስለው ሕዝብ የሚያማርሩ ማደያዎች ከነዳጅ ሥርጭቱ እንደሚታገዱና እንደሚታሸጉ ተገለጸ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳኅረላ አብዱላሂ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ፣ ከነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኮሚቴ ተቋቁሞ በማደያዎች ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ቁጥጥር እያደረገ ነው፡፡

በማደያዎች አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲቀረፉም ከማደያ ባለቤቶች ጋር ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡

ሕገ ወጥ ተግባር ለፈጸሙ ማደያዎችም ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር ክትትል በማድረግ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሀገር አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ምንም ዓይነት የነዳጅ እጥረት አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡

ከሚያዝያ 16 እስከ ትናንት ከ 115 ሺህ በላይ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ መፈጸሙን እና 223 ሚሊየን ብር መዘዋወሩንም ጠቁመዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ