Fana: At a Speed of Life!

በቦረና ዞን በ136 ሚሊየን ብር የጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ሁለት ወረዳዎች በ136 ሚሊየን ብር የጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ።

ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚከናወን ሲሆን፥ ቁፋሮውን የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እንደሚያከናውነው የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

የውል ስምምነቱን የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እና የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሉ ለማ ተፈራርመውታል።

አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በቦረና ዞን በተደጋጋሚ ድርቅ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ድርቁን ለመቋቋም ታሳቢ የተደረጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርቅን የሚቋቋምና ለአየር ንብረት የማይበገር የውሃ ልማት ስራ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአልወያ ወረዳ 3 ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በ90 ሚሊየን ብር እና በዋጨሌ ወረዳ 6 ጉድጓድ ከ46 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሉ ለማ በበኩላቸው የጉድጓድ ቁፋሮ ስራውን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለማስረከብ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.