Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ከ60 በመቶ በላይ የነዳጅ አቅርቦቷን ከአውሮፓ ኅብረት ወደ እስያ ልታዞር ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚህ ዓመት ሩሲያ ወደ ውጭ ከምትልከው ነዳጅ ከ60 በመቶ የሚልቀውን አቅርቦት ከአውሮፓ ወደ እስያ ልታዞር መሆኑን የሀገሪቷ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ኖቫክ ገለጹ፡፡

ሩሲያ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ምዕራባውያን ማዕቀብ መጣላቸውን ተከትሎ መሆኑን አር ቲ ዘግቧል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት በባሕር ሲቀርብላቸው የነበረውን የሩሲያ ነዳጅ መቀበል አቁመዋል፡፡

ከፈረንጆቹ ታኅሣሥ ወር ጀምሮ የአውሮፓ ኅብረት ፣ የቡድን 7 አባል ሀገራት እና አጋሮቻቸው ከሩሲያ በሚገባ ድፍድፍ ነዳጅ ላይ እገዳ እና በበርሜል እስከ 60 ዶላር የሚደርስ የዋጋ ጣሪያ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

ቀደም ሲል ሩሲያ ለአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ልትልክ ከነበረው 220 ሚሊየን ቶን ድፍድፍ እና የተጣራ የነዳጅ ምርቶች አቅርቦት ውስጥ 140 ሚሊየን ቶን ያኅሉን ወደ እስያ እንደምታዞርም አስታውቃለች፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምዕራባውያኑ ከ80 እስከ 90 ሚሊየን ቶኒ በቂ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

በፈረንጆቹ 2022 ላይ ሩሲያ ወደ ውጭ የምትልከውን የነዳጅ አቅርቦት በ7 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደጓን ዘገባው አመላክቷል።

በዚህም ወደ 242 ሚሊየን ቶን ነዳጅ ለውጭ ገበያ ስታቀርብ የላከችው የድፍድፍ ነዳጅ ምርት ደግሞ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሁለት በመቶ ጨምሮ 535 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን ደርሷል ነው የተባለው፡፡

ሩሲያ እየተቀየረ ከመጣው ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር ራሷን ለማጣጣም የኃይል አቅርቦቷን ‘ወዳጅ ሀገራት’ ወደምትላቸው ለማዞር ኮዝሚኖ የተሠኘውን ግዙፉን የሩቅ ምሥራቅ ወደቧን መጠቀም ጀምራለች፡፡

በእስያ-ፓሲፊክ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ሀገራት የሚደርሳቸው አቅርቦትም በዓመት ወደ 42 ሚሊየን ቶን ማደጉ ተመላክቷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.