Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከሕግ የራቁ የታጠቁ ሃይሎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ እየተሠራ ነው – የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከሕግ የራቁ የታጠቁ ኀይሎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
 
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡
 
የመግለጫው ሙሉ ቃል አንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
በሀገራችን የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን የክልላችን የፀጥታ ተቋማት አመራሩ እና አባሉ ከሰላም ወደዱ ህብረተሰብ ጋር በመመካከር ከእርስ በርስ ግጭት የመውጣት ባህል እንዲዳበር መንግስት ሆደ ሰፊ በመሆን ለሰላም በሩን በመክፈት በሰፊው ስራ እየሰራ ይገኛል።
 
በተለይም ከመጋቢት 5 /2015 ዓ.ም ጀምሮ የክልል ከፍተኛ አመራሮች በሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች በኢ-መደበኛነት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በሰላማዊ መንገድ በአካባቢያቸው በሰላም አስከባሪና ሚሊሻ ሰራዊት እንዲደራጁ በመንግስት ስምሪት ውስጥ መስራት የማይፈልግ ወደ ግል ስራው እንዲገባ ተከታታይ የውይይት መድረክ ፈጥረናል።
 
መንግስት ህግ ለማስከበር አቅም ሳያንሰው የሰላም ውይይትን በማስቀደሙ የክልሉን መንግስት አመራር አልባ ለማድረግ በህቡእ በመደራጀት አሰቃቂ ግድያ እየተፈፀመብን ይገኛል። ህግ ለማስከበር የገባውን የሐገር መከላከያ ሰራዊት ያልሆነ ስም በመስጠት ለህብረተሰቡ የጥላቻ መንፈስ ለመፍጠር የበሬ ወለደ ታሪክ በማህበራዊ ሚዲያ ሲቀሰቀስ ይውላል።
 
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለአማራ ክልል ህዝብ ህይወቱንና ደሙን የሰጠ በችግር ጊዜ አብሮ መከራ ያየ የአማራ ክልል ህዝብም ለመከላከያ ሰራዊታችን ፍቅሩንና አለኝታነቱን በተግባር ያሳየ አብሮት የሞተ የደማ እውነተኛ ሰራዊቱን የሚያከብር ህዝብ ነው።
 
ተከፋይ አክቲቪስቶች የሀሰት ትርክት ሳንሰማ ለህግ መከበር ህዝባችን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።
 
የክልሉ መንግስት ከሀገር ሽማግሌዎች ከሃይማኖት አባቶች ጋር አብሮ በመስራት ከህግ እርቀው የነበሩ የቅማንት ታጣቂዎችን በሰላማዊ መንገድ ወደ ቀበሌያቸው እንዲገቡ ተደርጓል። በዘህም ከጎንደር መተማ መስመር ሰላማዊ እንቅስቃሴን መፍጠር ተችሏል፡፡
 
በሰሜን ወሎ ዞን የሚንቀሳቀሱ የምስራቅ አማራ ፋኖ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ቢያደርሱም አፀፋዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በሀገሩ ባህል መሰረት በዘወልድ ሽማግሌዎች መንግስት ይቅር ብሎ ለሰላም እጁን በዘረጋበት ወቅት በዚህ ሃይል የሚመራው ቡድን አመራራችን በመግደል አሁንም ህዝቡን እያሸበረ መከላከያ ሰራዊታችን ከህዝብ ለመነጠል እየሰራ የሚገኝ በመሆኑ፣ አጥፊዎች ለህግ እስኪቀርቡ የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ መላው የፀጥታ መዋቅራችንና ህዝባችን ለህግ የበላይነት መከበር ዘብ እንድትቆሙ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
 
የክልሉ መንግስት የነፍስ ወከፍ ጦር መሳሪያ የማስወረድ ፍላጎት ሳይሆን ህጋዊ የማድረግ መሆኑን በተደጋጋሚ የማሳወቅ ስራ ሰርተናል፡፡
 
በጦር መሳሪያ አዋጅ መሰረት የቡድን ጦር መሳሪያ በማንኛው መንገድ ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልና ለመንግስት ገቢ የሚደረግ መሆኑን በመገንዘብ ሚያዚያ 23/2015 ዓ ም በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በጃዊ ወረዳ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለመንግስት ሰጥተዋል።
 
ዳግም በወንጀል ድርጊት ታርቀውና ካሳ ከፍለው ተሳታፊና ተባባሪ እንደማይሆኑ አምነው በግል ከበደሉት ግለሰብ ጋር ታርቀውና ካሳ ከፍለው ከህዝብና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲገቡ የሚያስችል ስራ የምንሰራ ይሆናል።
 
በመጨረሻም ለህግ መከበር መላው ህዝባችን ከክልሉ የፀጥታ ሃይልና ከሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ጎን በመቆም ትብብር እንድታደርጉ እየጠየቅን፣ ህገ ወጥ በመሆን በቡድን ታጥቆ መንቀሳቀስ በግድያና በዘረፋ የህዝባችንን ሰላም የምትነሱ ሃይሎች በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት እጃችሁን ከመስጠት ውጭ አማራጭ የሌለ መሆኑን አውቃችሁ እድሉን እንድትጠቀሙበት ጥሪ እናስተላልፋለን።
 
የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ
 
ሚያዚያ 24/2015 ዓ.ም
 
ባሕርዳር
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.