Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ክልል አቀፍ 4ኛ ዙር የተቀናጀ የኮቪድ-19 እና የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሄደ፡፡

የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባቱ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡

ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆናቸው ልጃገረዶች  ነው የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባቱ  እየሰጠ ያለው፡፡

በዚህም ከ400 ሺህ በላይ ሴቶች የማህፀን በር ጫፍ መከላከያ ክትባት እንዲያገኙ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ 4ተኛው ዙር የተቀናጀ የኮቪድ-19 ክትባት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡

የኮቪድ ክትባቱም ከ12 ዓመት በላይ ለሆናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ይሰጣል ነው የተባለው፡፡

በዚህም ከ3 ሚሊየን የሚበልጡ ዜጎች 4ኛውን ዙር የኮቪድ -19 ክትባት እንደሚወስዱ ነውየተገለጸው፡፡

ከኮቪድና ከማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት በተጨማሪ ምንም ክትባት ያልተከተቡና ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ሕጻናትን የመለየትና ክትባት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ይከናወናል፡፡

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች ሕፃናትና ሥርዓተ ምግብ አገልግሎት ዳይሬክተር ተስፋዬ ሌጂሶ እንዳሉት÷ የወጣቶች እንዲሁም አፍላ ወጣቶች ጤና የምክር አገልግሎት እና ሌሎች ተግባራት በቅንጅት ይሰራሉ፡፡

የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማሙሽ ሁሴን÷  የተዘጋጀውን ክትባት መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በክልሉ በሁሉም ጤና ተቋማት፣ ውሎ ገብ እና ተንቀሳቃሽ ሳይቶች ላይ ክትባቱ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡

በብርሃኑ በጋሻው እና ኡስማን መሐመድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.