Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋገጠ፡፡

ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም 27 የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሕብረቱ ከፍተኛ ተወካይ (የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት) ሊቀ መንበርነት ባደረጉት ስብሰባ÷ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ቀስ በቀስ ወደ መደበኛ ደረጃ ለማድረስ አዲስ እና መሰረታዊ መደምደሚያዎችን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

ውሳኔው በሕብረቱ እና በኢትዮጵያ መካከል ባለው አጋርነት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ለአውሮፓ ሕብረት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኗም ተጠቅሷል፡፡

በመሆኑም የአውሮፓ ሕብረት ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ ሰላም በሚወስደው መንገድ ላይ የምታደርገውን ተጨማሪ መሻሻል ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

ስለሆነም በእነዚህ አዲስ የፖሊሲ መደምደሚያዎች ሕብረቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ለተፈረመው ዘላቂ የጦርነት ማስቆም የሰላም ስምምነት ሙሉ ድጋፉን ገልጿል።

የስምምነቱን ትግበራ ቀጣይነት መሰረት በማድረግም÷ የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከጠንካራ የፖለቲካ እና የፖሊሲ ውይይት ጋር መደበኛ በማድረግ ወደ ሙሉ እና የተጠናከረ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት እንዲመለስ እንደሚያደርግ አመላክቷል፡፡

በዚህ አውድ ውስጥ በተለይ ተጠያቂነት እና የሽግግር ፍትህ አስፈላጊ መሆናቸውንም ነው ሕብረቱ የገለጸው፡፡

የአውሮፓ ሕብረት የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ የወጣውን ግሪን ፔፐር (Green Paper) በመቀበል የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መመዘኛዎች እና ደንቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ በውስጡ የተካተቱትን አማራጮች በማሻሻል ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ ያበረታታል።

በምክር ቤቱ መደምደሚያ ላይ የአውሮፓ ሕብረት በአብዛኛዎቹ ግጭት በተከሰተባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በቅርቡ የተሻሻለውን ሰብዓዊ አገልግሎት አቅርቦት በደስታ እንደሚቀበለውም ነው የተመለከተው፡፡

በከባድ ድርቅ እና ሌሎች ቀውሶች የተጎዱትን ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ጨምሮ የተስፋፋው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎቶች በቂ እና የተቀናጀ ምላሽ የሚሹ መሆናቸውንም እንደሚያምንም አስታውቋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የኦሮሚያና የአማራ ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ጥቃቶች የአውሮፓ ሕብረትን በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት ግልፅ፣ ሁሉን አቀፍ፣ አካታች እና ሕዝብን ያማከለ ብሄራዊ የውይይት ሂደት እንዲቀጥል የአውሮፓ ሕብረት ጠይቋል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ የግጭት አፈታት፣ ዕርቅ እና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን በማጠናከር ላይ ተጨማሪ መሻሻል እንዲኖር የአውሮፓ ሕብረት መደበኛ የባለ ብዙ-ዓመት የልማት አመላካች መርሐ ግብሩን (EU MIP) እንደገና ለመጀመር ዝግጁ መሆኑንም ነው ያስታወቀው፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.