Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ የማዕድን አዋጅ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን የሚያበረታታ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ የወጣው የማዕድን አዋጅና በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው ፖሊሲ ለዘርፉ ልማት የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን የሚያበረታታ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከክልል የዘርፉ ኃላፊዎች ጋር ምክክር አድርጓል።

የማዕድን ሚኒስትር ሐብታሙ ተገኝ (ኢ/ር)÷ የማዕድን ዘርፉ በተለይም በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና አጠቃላይ ለሀገራዊ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ለዘርፉ ልማት መሳካት ከባንኮች፣ ከጸጥታ አካላት፣ ከክልል ኃላፊዎችና ሌሎች ተቋማት ጋር የጋራ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

በማዕድን መገኛ አካባቢዎች የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥነት ለመከላከል የጥበቃና ቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የማዕድን አምራቾች ወደ ዘርፉ ልማት በስፋት እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

አዲስ የወጣው የማዕድን አዋጅና በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው የማዕድን ፖሊሲ ለዘርፉ ልማት የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን በስፋት የሚጋብዝና የሚያበረታታ መሆኑን አብራርተዋል።

የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት፣ የአመራረት ሂደቱን ማስተካከልና ምርቱን ወደ ገበያ በስፋት የማቅረብ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላሉ ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.